TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
205 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ከደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፦

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የክልሉን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሰጡት ህገ-መንግስታዊ የሥልጣን ውክልና ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ሕዝቡን በማስተባበር እና በክልሉ ውስጥ ያለውን እምቅ የልማት ፀጋዎች እንዲሁም ውስን የሆነው የካፒታል አቅሞች አቀናጅቶ በመምራት አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን ሕዝቡም በየደረጃው
ተጠቃሚ መሆን ስለመቻሉ ሕዝቡ ራሱ የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በርካታ ያልተፈቱ የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ያሉት መሆኑን ደኢህዴን በተገቢ ሁኔታ ይገነዘባል፡፡
በአገር ደረጃ ለመጣው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ደኢህዴን ከፍተኛ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመራ እና ሕዝቡም በለውጡ የተሟላ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ አበክሮም ይሰራል፡፡

በ10ኛው የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸማቸው የደረሰበትን ደረጃ የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር ገምግሟል፡፡ ከጉባኤ ማግስት ጀምሮ
በኃላፊነት መንፈስ መፍትሄ እና ምላሽ ማግኘት ያለባቸውን ጥያቄዎች በድርጅቱ መሪነት እየተፈጸመ ያለበትን ሁኔታ ፈትሸዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው እና ማዕከላዊ ኮሚቴው በዝርዝር የገመገማቸውን ጉዳዮች እና በቀጣይ ወራት ርብርብ ማድረግ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ በየደረጃው ከሚገኘው የደኢህዴን አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1/07/2011 ዓ.ም በክልሉ ርዕሰ መዲና ሀዋሣ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ውይይቱ በሰከነ ሁኔታ እየተካሄደ ባለበት የተወሰኑ በብድን የተደራጁ አካላት ውይይቱ አዳራሽ ጭምር በመግባት ህግንና ሥርዓትን ባልተከተለ አግባብ የውይይት መድረኩ እንዲታወክ፣ እንዲቋረጥ እንዲሁም
በአንዳንድ አመራሮች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል፡፡ ድርጊቱን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት በጽኑ ያወግዛል፡፡ ሁኔታው ወደ ከፋ ጫፍ እንዳይደርስ የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች ያሳዩትን ኃላፊነት የተሞላበት ትዕግስትና ጨዋነት የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ያደንቃል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የተዘጋጀውን ሰነድ አስመልክቶ #የተሳሳቱና #የተዛቡ መረጃዎች ለህብረተሰቡ እየተላለፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሰነዱ የትኛውንም የሕዝብ ሁኔታ በአሉታዊና በነቀፌታ የማይገልጽ የድርጅትና የመንግስት ስራዎችን የሚዳስስ፣ በድርጅቱ አሰራርና አካሄድ መሰረት መስተካከልና መጥራት የሚገባቸውን ጉዳዮች፣ የተከሰቱ ችግሮችና መፍትሄዎችን በተገቢው ሁኔታ የሚያሳይ ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም ደኢህዴን የሕዝቦቻችንን ቱባ ባህልና እሴቶቻቸውን የሚያከብር የታገለለትንና በክልላችን እየደመቀ የመጣውን የሕዝቦችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም ማንነት፣ ቋንቋ፣ እና ትውፊት አክብሮ የሚንቀሳቀስ ሕዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ለዚህም ሁልጊዜ ጽኑ አቋምና የጠራ መስመር ያለው ድርጅት ነው፡፡

ሰነዱ በድርጅቱ ባህል መሰረት ዝርዝር ጉዳዮች #የተፈተሹበትና ችግሮችን አንጥሮ ያወጣ ሰነድ ሲሆን ሰነዱ ላይ የተመላከተው ዝርዝር ግምገማ ያልጣማቸው ግለሰቦች የሚፈጥሩት #ውዥንብር እንደሆነ ደኢህዴን ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ይህ ሰነድ ለበርካታ ቀናት በደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዘንድ የሰላ #ውይይት ተደርጎበትና በሁሉም ዘንድ የጋራ መግባባት ተደርሶበት የተዘጋጀ ሰነድና የዳበረ በቀጣይም የድርጅትና የመንግስት ሥራዎችን በክልላችን በሰከነ አግባብ ለመምራት እንዲሁም የክልላችን ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅምና መብት የሚያስጠብቅ ሁኔታ ከሁሉም የክልላችን አመራሮች ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና በቀጣይ ለመስራት የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑን በአጽንኦት ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

የሲዳማ ሕዝብ ባለው #ኩሩ እና #ቱባ ባህላዊ እሴቶች በባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከሌሎች የክልሉ ሕዝቦች ጋር አብሮ የመኖር የዳበረ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ያለው ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ የሲዳማ ብሔር ሌሎች ሕዝቦችን "ዳኤቡሹ" ብለው ተቀብሎ አቅፎ የሚኖር፣ የሚያስተናግድ ታላቅ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው፡፡ ደኢህዴንም ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ከፍተኛ አክብሮት አለው፡፡
ሕዝቡም በደኢህዴን መስመር ተጠቃሚ በመሆኑ ኩራት ይሰማዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሕዝቡን የማይወክሉ የተወሰኑ ቡድኖች እየተካሄደ የነበረውን የውይይት መድረክ እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡ የትኛውም ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሰለጠነ መንገድ መስተናገድ ሲገባው የኃይል እርምጃን አማራጭ በማድረግ የሚቀርብ ጥያቄ ተቀባይነት የሌለውና ተገቢነት የጎደለው በመሆኑ ደኢህዴን ያወግዛል፡፡ ሕግን የተላለፉ አካላትንም መንግስት ተከታትለው ለሕግ እንዲያርብ ይጠብቃል፡፡ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ፣ በነጻነት የመዘዋወር እና የመሰብሰብ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡

በሀዋሳ እና በሲዳማ ዞን የሚትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ኃይማኖት መሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና መላው የህብረተሰብ አባላት ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ላሳያችሁት ትዕግስትና ጨዋነት ለተሞላበት ኃላፊነት ደኢህዴን አድናቆቱን ያቀርብላቸኋል፡፡ ይኸው አርአያነት ያለው ተግባራችሁ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ደኢህዴን ሙሉ እምነት አለው፡፡

በውይይቱ መሰነካከልና መስተጓጎል ምክንያት የተረበሻችሁ አመራሮች ድርጅታችሁ ደኢህዴን ታላቅ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ የተቋረጠው ውይይትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ደኢህዴን ያረጋግጣል፡፡ በውይይቱ የሚቀመጡ አቅጣጫዎች ለክልላችን ሕዝቦች ተጠቃሚነታቸውና ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ደኢህዴን ወትሮኑም ፈተናዎችን ተጋፍጦ እንደሚያልፈው ሁሉ በቀጣይ ጊዜ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለመላው አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን እንዲሁም ለክልላችን ሕዝቦች ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት
የካቲት 29/2011 ዓ.ም
ሀዋሣ

@tsegabwolde @tikvahethiopia