TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.7K photos
1.44K videos
207 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
በኦሮሚያ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ‼️
(20/80ና 40/60)

የ20/80ና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ይፋ ከመሆን ጋር ተያይዞ ቦታው የኦሮሚያ ነው በሚል ከ10 በላይ በሚሆኑ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የተገነቡባቸው አካባቢዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሆነው የአዲስ አበባ መስተዳድር ውሳኔ የሚያሳልፈው እንዴት ነው፤ ለተፈናቃዮቹ አርሶ አደሮች የተሰጠው ካሳ እዚህ ግባ የማይባል ነው፤ የተቀናጀው ማስተር ፕላን ቅጥያ ነው የሚሉ ሀሳቦችን ተቃዋሚዎቹ አንስተዋል።

#በምስራቅ_ኦሮሚያ ጪሮ ከተማ ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ሰልፈኛ " በዚህ ተቃውሞ ላይ ዋነኛ መልዕክታችን በአዲስ አበባ አካባቢ ያሉት መሬቶች ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ሊመለስ ይገባል" የሚል ነው። ተቃዋሚው ጨምሮም ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነው አወዛጋቢው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሊመለስ አይገባም ብሏል።

ተቃውሞዎቹ በሻሸመኔ፣ ጪሮ፣ ጂማ፣ አሰላ፣ አዳማና ሂርና ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተስፋፉ ሲሆን በሻሸመኔ አካባቢ የሚገኙ ሰልፈኞች "ኦዲፒ ያልነውን ረስታችሁታል፤ መሬታችን የደም ስራችን ነው" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ነበር።

በትናንትናው ዕለት 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የዕጣ ማውጫ ስነ ስርአት ለተጠቃሚዎች የተላለፈ ሲሆን፤ ከአካካቢው ለተነሱ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ያለ እጣ እንዲሰጣቸው በከተማው አስተዳደር ካቢኔና በቤቶች አስተዳደር ውሳኔ መሰረት ያለ ዕጣ እንዲተላለፍ መወሰኑን ምክትል ከንቲባ #ታከለ_ኡማ በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሲገነቡ የተጎዱ ሰዎች እንዳሉ ያልደበቁት ምክትል ከንቲባው "በተለይም የእርሻ መሬታቸውን ለነዚህ ተግባራት ሲሉ የለቀቁና ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ የተዳረጉ የአርሶ አደር ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ህመማችሁ የእኛ መሆኑን እንድታውቁ" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባው ይህንን ቢሉም ኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ ለረጅም ጊዜ ለዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለትና ከ2006 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ቅጥያ ነው የሚሉ ትችቶችም እየተሰሙ ነው።

ምንም እንኳን የተቀናጀው ማስተር ፕላን ከፍተኛ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ውድቅ ቢደረግም የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባና ኦህዴድ ሊቀ መንበር አቶ ኩማ ደመቅሳ ጉዳዩ ከመፈናቀል ጋር አብሮ ስለመጣ እንጂ "ተራማጅ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ማስተር ፕላኑ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል" ብለው ለቢቢሲ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ምንም እንኳን ከመንግሥት በኩል ምንም አይነት መግለጫ ባይሰጥም በቅርቡ ከውጭ ሀገር የተመለሰው የተባበሩት ኦነግ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ያለውን ድንበር መወሰን ያለበት የኦሮሚያ ክልል ነው የሚል ነው።

በ13ኛው ዙር የ20/80 ቤቶች 32ሺ 653 ቤቶችና በ2ኛ ዙር የ40/60 ቤቶች ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 1ሺ 248 ስቱዲዮ፣ 18ሺ 823 ባለ አንድ መኝታ፣ 7ሺ 127 ባለሁለት መኝታ እና 5ሺ455 ደግሞ ባለ ሶስት መኝታ መሆናቸው ተገልጿል።

በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ የሚካተቱትም በ1997 ተመዝግበው በ2005 ዓ.ም በነባር መደብ የተመዘገቡና በ2005 ዓ.ም የአዲስ ባለ ሶስት መኝታ ተመዝጋቢ ደንበኞች መሆኑ ተገልጿል።

Via BBC አማርኛ
@tsegabwolde @tikvahethiopia