TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.8K photos
1.44K videos
207 files
3.99K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#የካቲት2010

የ2010 ዓ/ም በተለይም የካቲት ወር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት ፤የካቲት 8 ደግሞ ታሪካዊ ቀን ተብሎ ሊመዘገብ የሚችል ነው።

ለረጅም ዓመታት በእስር ቤት እንዲማቅቁ የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ በርካታ ወጣቶች ከእስር እንዲፈቱ የተደረገበት ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡበት ወር ነው።

ከብዙ ትውስታዎች በጥቂቱ ፦

- መላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ የነበረችበት ወቅት ነበር።

- በበርካታ ከተሞች በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና አማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል የወጣቶች የ #ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ላይ ተቃውሞ እጅግ የበረታበት ነበር። ተቃውሞው እስረኞች እንዲለቀቁ፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ መንግስት ዜጎችን መግደል እንዲያቆም ሲጠየቅበት የነበረ ነው።

- በተለይ በኦሮሚያ ክልል እጅግ በርካታ ከተሞች ፣ በአማራ ፣ በደቡብ ክልሎች በሚገኙም ከተሞች መንግስትን በመቃወም የስራ ማቆም እና ቤት የመቀመጥ አድማ የተደረገበት ወር ነበር።

- መንግስት እስረኞችን ለመፍትታ የወሰነበት በዚህም ፦ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ (በወቅቱ) ጉዳያቸው በህግ ተይዞ የነበሩ 329 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ የወሰነበት በአጠቃላ 746 እንዲፈቱ የተባለበት ወር ነበር።

- እነ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ፣ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ አቶ አበበ ቀስቶ እና አቶ እስክንድር ነጋ የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ አንፈርምም ያሉበት ወር ነው።

- ከሰባት እስከ ሃያ ሁለት አመታት እስር የተበየነባቸው የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አንዳችም ያጠፋነው ጥፋት የለም በሚል "የምንጠይቀውም ይቅርታ የለም " የይቅርታ ፎርም አንፈርምም ያሉበትም ወር ነው።

- የ2010 የካቲት ወር የኦፌኮው ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ፣ አቶ ጉርሜሳ አያና፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጌቱ ጋሩማ፣ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ ከእስር የተለቀቁበት ነው።

- የዞን ዘጠኞቹ (የቀድሞ) እነ አቶ በፍቃዱ ኃይሉ ፣ አቶ አጥናፍ ብርሃኔ እና አቶ ናትናኤል ፈለቀ ክስ የተቋረጠበት ወር ነበር የካቲት 2010 ዓ/ም።

- እነ አቶ አዱአለም አራጌ ፣ አቶ እስክንድር ነጋ ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ፣ አቶ ኦልባና ለሌሳ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ ፣ አርቲስት ሴና ሰለሞን ፣ አርቲስት ኤልያስ ክፍሉ ፣ ወ/ሮ ጫልቱ ታከለ ፣ ወ/ሮ እማዋይሽ ፣ አቶ ማሙሸት አማረ፣ ኦኬሎ አኳይ (የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት)፣ አቶ አንዱአለም አያሌው ፣ እነ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ ከእስር የተለቀቁበት ወር ነበር።

* የካቲት 8 / 2010 (በዛሬዋ ቀን) የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡበትና ይህንኑም በመግለጫ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳወቁበት ቀን ነበር።

- በ2010 የካቲት ወር የሚንስትሮች ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በሁሉም ሀገሪቱ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነበት እና ወደ ምክር ቤት የመራበት ነበር።

- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባ የካቲት 23/2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ታእቅቦ ያፀደቀበት። በኃላም የተፈጠረው የቁጥር ስህተት መነጋገሪያ ነበረበት በወቅቱ አፈጉባኤ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ህዝብን " ይቅርታ " የጠየቁበት ወር ነበር።

- የአዋጁ መታወጅ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲከሰት ያደረገም ነበር። በነበሩ ግጭቶች ቀደም ብሎ በወሩ ውስጥ በነበሩ ተቃውሞዎች በርካታ ወጣቶች የተገደሉበት ነበር።

- የአማራ ክልል በጎንደርና ጭልጋ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የ224 ተጠርጣሪዎች ክስ ያቋረጠበት።

- የጎንደሯ ወጣት ንግስት ይርጋ ከእስር የተፈታችበት ወር ነው (የካቲት 13 ቀን 2010) ።

- የኢትዮጵያ መንግስት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን (አሁን በህይወት የሉም) ጨምሮ 18 ሰዎች በይቅርታ እንዲፈቱ የወስነበት ወር ነው።

- የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደርገዋል ተብለው የተከሰሱት ኮሎኔል አንተነህ ደምስ፣ ኮሎኔል አለሙ ጌትነት፣ ብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ (አሁን በህይወት የሉም)፣ ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ ከእስር የተፈቱት በዚሁ የካቲት ወር ነው።

- የኦህዴድ (የቀድሞ የኢህአዴግ አባል ድርጅት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠበት ወር ነው። (ዶክተር ዐቢይ የአሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር /የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዜዳንት ናቸው)

- ሱማሌ ክልል 1500 እስረኞችን ከእስር የፈታበት ነው።

- የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከእስር የተፈቱበት ወር ነው። እሳቸው ሁለት ጊዜ "ፈርመው እንዲወጡ" ተብሎ ሲጠየቁ ወንጀል እንዳልፈፀሙ በመግለፅ የይቅርታ ፎርም ላይ አልፈርምም ብለው ነበር። (አሁን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው)

(ከላይ የዘረዘርናቸው በቲክቫህ ኢትዮጵያ ገፃችን በየካቲት ወር 2010 ላይ ከተለዋወጥናቸው በርካታ መረጃዎች / በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት በወሩ ውስጥ ከታዩ ክስተቶች ጥቂቶቹን ያስታወስንበት ነው)

#TikvahFamily

@tikvahethiopia