TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ሶስት ዓመት ያለ መብራት . . .

• " የመብራት መቋረጥ የከፋ የኢኮኖሚ ችግር እየፈጠረብን ነው ፤  ስራ የነበራቸው ሁሉ ስራ ፈላጊ ሆነዋል " - ነዋሪዎች

• " ችግሩ ከወረዳው መንግስት አቅም በላይ ነው። የዞንና የክልል አመራሮች በአስቸኳይ መልስ ይስጡን " - የከለላ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ታደሰ

ለሶስት ዓመታት መብራት የተቋረጠባት የከለላ ወረዳዋ ከተማ ነዋሪዎች የመፍትሄ ያለ እያሉ ይገኛሉ።

በከለላ ወረዳ የ01 ደገር ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት የመብራት አገልግልት በመቋረጡ የከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የከተማ ነዋሪዎቹ አገልግሎት እየሰጠ የነበረው መብራት ከሶስት ዓመት በፊት መቋረጡን ገልጸው በዚህ ምክንያት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ማለትም ፦
- በብረታ ብረትና ጣውላ ስራ፣
- በምግብና ሻይ ቤቶች
- በጸጉር ቤቶች ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች #ስራቸውን_አቋርጠው ስራ ፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት የመብራት አለመኖር በሚያከናውኑት የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንደፈጠረባቸውና #የኑሮ_ውድነት እንዲባባስ በማድረግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ እንዳደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

የወረዳው መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን እንዲፈታላቸውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ይህንን በተመለከተ የከለላ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ታደሰ ፤ በከተማዋ የመብራት አገልግሎቱ መቋረጥ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረና በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ሲሆን የወረዳው መንግስትም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከዞን እስከ ክልል ድረስ በማነጋገር መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሉን ጥረት ሲያደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

" የመብራት መቆራረጡ በከተማው ነዋሪዎች እና በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ " ነው ያሉት ኃላፊው ችግሩ ከወረዳው መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የዞን እና የክልል አመራሮች በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጡ አቶ ሁሴን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መረጃው ከከለላ ወረዳ ኮሚኒኬሽን የተገኘ ነው።

@tikvahethiopia @tikvah_Eth_BOT
" ዜጎች አሁን በየዕለቱ እያሻቀበ ባለው #የኑሮ_ውድነት ራሳቸውን ሊያኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ አገርንም አደጋ ላይ ይጥላል " - ኢሰማኮ

የሰራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የመትከል ጥያቄ እየተንከባለለ የመጣና የኢትዮጵ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ጭምር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረበበት በኢትዮጵያ ያሉ ሠራተኞችን ለምሬት የዳረገ ግን ምላሽ ያልተቸረው ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ሲያወሱ ይደመጣሉ።

ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ያቀረቡ አንድ ሠራተኛ ፤ " በአዲስ አባባ ከ3,000 ብር በታች የቤት ኪራይ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። ለዛውም በኮምፒስታቶን የተጠጋገነ ቤት ነው። የወር ደመወዜ ደግሞ 3,000 ብር ነው። ታዲያ በዚህ ደመወዝ እንዴት መኖር ይቻላል ? " ሲሉ አማረዋል።

አክለውም ፤ " ምንም እንኳ ለኑሮ ውድነቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የደመወዝ ወለል አለመተከልም አንዱና ዋነኛው መንስኤ ነው። በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም መንግሥት ግን የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከማድረግ በዘለለ መጽትሄ እየሰጠ አይደለም " የሚል ወቀሳ አቅርበዋል።

እኝህን ቅሬታ አቅራቢ ለአብነት ጠቀስን እንጂ እሮሮው በበርካቶች ዘንድ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል። 

የቅሬታ አቅራቢዎችን እሮሮ መነሻ በማድረግ ቲክቫህ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) የስራ አስፈፃሚ አባል እና የኢንድስትሪ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዲርብሳ ለገሰ ተከታዮቹን ጥያቄዎች አቅርቧል።

* የኑሮ ውድነት በየዕለቱ እየጨመረ በሚስተዋልበት ሁኔታ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጥያቄ ግን ከቀጠሮ ባለፈ ለምን መፍትሄ አይሰጠውም ?

* ጉዳዩን በተመለከተ ከዚህ በፊት ለጠ/ ሚኒስትሩ ያቀረባችሁት ጥያቄ አሁንስ ከምን ደረሰ ?

* ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጥያቄ መፍትሄ ሳይሰጠው እየተንከባለለ የመጣ ጥያቄ ነው። አሁንስ ቢሆን እየተንከባለለ እንደማይቀጥል በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል ?

* ጠቅላይ ሚኒስተሩ አቅጣጫ የሰጡበት ጉዳይስ በተግባራዊነቱ ምን ያክል እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አቶ ዲርብሳ ለገሰ ምን ምላሽ ሰጡ ?

- ለኑሮ ውድነት የራሱ የሆነ ፋክተር ስላለው ይኸኛውም አንደኛው ነው በሚል አንስተንላቸዋል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ። በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ የከበደው ቢኖር ሠራተኛው ነው። 

- የዚህ ጥያቄ እየተንከባለለ መሄድ ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው አገርንም ይጎዳል በእኛ እምነት ለማንም አይጠቅምም።

- ዜጎች አሁን በየዕለቱ እያሻቀበ ባለው የኑሮ ውድነት ራሳቸውን ሊያኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ #አገርንም_አደጋ_ላይ_ይጥላል

- ይህ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ እንዲኬድበት አቅጣጫ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በተለያዩ የሥራ መደራረብ ምክንያቶች አቅጣጫውን የተቀበሉ አካላት ባለመኖራቸው ነው እንጂ ባሉበት ቦታ ሆነው ክትትል እያደረግን እንገኛለን።

- በኢትዮጵያ ለኑሮ ውድነቱ የሠራተኛ ደመወዝ ማነስ ብቻ አይደለም። የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ግን ይህም እንደ አንድ ፋክተር ስለሚሆን ይህንንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተናል።

- በኢትዮጵያ #ሰላም_እስከሌለና #ሰላም_መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ ለኑሮ ውድነት በሌላ መንገድ ተገቢና ዘላቂ ምላሽ መስጠት ይገባል ተብሎ አይገመትም። 

- አሁን ሠራተኞች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል። #መፈናቀል#መንገላታት ይደርስባቸዋል።

- መዘግየቱ ተገቢነት እንደሌለው ፣ ጉዳቱም ለሁላችን እንደሚሆን መንግሥትም ሊገምተው እንደሚገባ በየዕለቱ፣ በየጊዜው ማሳሰባቸን አይቀርም፣ ክትትል እናደርጋለን ውጤቱንም እናሳውቃችኋለን።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ከሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ባገኘው መረጃ ፦

* ሚኒመም ዌጅን በተመለከተ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ።

* #ዓለም_አቀፍ_አማካሪዎችንም ጭምር በማካተት ልምዶችንና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለማስታረቅ የሚችያስችል ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ሲጠናቀቅ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መረጃ ይሰጣል።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል #ያልተተከለላቸው አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት (3) የአፍሪካ አገራት ብቻ ሲሆኑ ፣ የሠራተኞች የመነሻ የወለል ደመዎዝ ተጠንቶ የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም በ2011 ዓ.ም በወጣው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ላይ ተደንግጓል።

ኢሰማኮ ፦
° ጥናት በማጥናት ለሥራና ክህሎት ጨምሮ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በደብዳቤ ቢያቀርብም መፍትሄ እንዳልተሰጠው፣
° በ2015 ዓ.ም የሜይዴይ በዓል ጥያቄውን ሰላማዊ መልስ እንዲሰጠው በሰላማዊ መንገድ ለማንሳት ቢሞክርም ሰልፉ እንደተከለከለ፣
° ባሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርጎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  አቅጣጫ እንዳስቀመጡ መግለጹ የሚታወስ ነው።

መረጃው በአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia