TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.95K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
መከላከያ‼️

ድሬዳዋን ሰላምና ፀጥታ #አስተማማኝ በማድረግ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚሰራ #በምስራቅ_ዕዝ_መከላከያ የሚመራው ጊዜያዊ የፀጥታ ጥምር ኮሚቴ አስታወቀ።

ኮሚቴው ምሽት ላይ በሰጠው #መግለጫ #በመልካ_ጀብዱ የሞቱት ሁለት ሰዎች ሰሞኑን ከተከሰተው የወጣቶች  ተቃውሞና ሰልፍ ጋር አይገናኝም፡፡

ጊዜያዊው የፀጥታ ጥምር ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ሰሞኑን ሁከትና ተቃውሞ የተነሳባቸው አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ ሰፍኖ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንደወትሮው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ኮሚቴው ገለልተኛ ሆኖ የህግ የበላይነት ማረጋገጥና የህዝብ ሰላምና ደህንነት የመጠበቁን ተግባራት በቋሚ ስፍራዎች ሰራዊት በመመደብና  በተንቀሳቃሽ መኪኖች በመታገዝ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የጥምር ኮሚቴው አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው አስረስ “በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ሁለት መቶ ተጠርጣሪዎች መካከል ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙት እየተለቀቁ ናቸው” ብለዋል።

ሌሎቹን መርማሪዎች ቃል እየተቀበሉ ይገኛሉ፤መረጃና ማስረጃ እየተሰባሰበባቸው በመሆኑ ይህ እንደተጠናቀቀ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለዋል፤ ታዳጊ ወጣቶች ተገቢው ምክርና ትምህርት ተሰቷቸው መለቀቃቸውንም ተናግረዋል።

ጂቲ ዜድ በተባለ ስፍራ በተካሄደው ሁከትና ብጥብጥ ሶስት ሸጉጥና ሁለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ መያዙን ተናግረዋል።

የጥምር ኮሚቴው አባል የፌደራል ፖሊስ የምስራቅ ክላስተር ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው “ትላንት በመልካ ቀበሌ የተከሰተው ግጭት አስቀድሞም ለዓመታት የዘለቀና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሲፈጠር የነበረ እንጂ ከሰሞኑ ችግር ጋር አይገናኝም” ብለዋል፡፡

በግጭቱ ወደ አዲሱ ምድር ባቡር ሰው ሊያደርስ ሲጓዝ የነበረ ወጣት የታክሲ ሹፌርና አንድ ሌላ ሰው መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወንጀሉን የፈጸሙ አምስት ሰዎች በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልፀው ሌሎቹንም በቁጥጥር ሥር የማዋል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

የፀጥታ አካሉ በድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት የጀመረው ሥራ ስኬታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የኮሚቴው አባል የድሬዳዋ ፍትህ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው፡፡

ችግሩ ከኃይማኖትና ከብሔር ግጭት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው አስረድተው ለዚህም ሌት ተቀን የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

“አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ከሰፈነ በኋላ የፖለቲካ አመራሩ የወጣቱን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመፍታት ስራ ያከናውናል” ብለዋል፡፡

የጥምር ኮሚቴው ሰብሳቢ የምስራቅ ዕዝ የኢንዶክትሬሽንና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ፍስሃ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው ፀጥታው አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት  እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ
@tsegabwolde @tikvahethiopia