TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.91K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ሆሮ ጉዱሩ~ወለጋ‼️

በኦሮሚያ ክልል በሆሩ ጉድሩ ወለጋ ዞን በሻምቡ ከተማ በርካታ ሰዎች #እየታሰሩ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ። በትላትናው ዕለት በተደጋጋሚ ለእስራት የተዳረገችው #ጫልቱ_ታከለን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና እስሩ ዛሬም መቀጠሉን ተናግረዋል።

በምዕራብ አሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመከላከል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ትላንት እንዳስታወቀው በሰዎች ሞት እና መፈናቀል የተጠረጠሩ 171 ግለሰቦች የሆሮ ጉድሩ ዞንን ጨምሮ በምዕራብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።

የሻምቡ ከተማ ነዋሪ እንደገለጹት በከተማይቱ ከአንድ ሳምንት በላይ በእስር የቆዩ ሰዎች አሉ። በሆሮ ጉድሩ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ እና ጃንሜዳ በተባለው የከተማይቱ ስፍራም ወጣቶች ተይዘው እንደሚታሰሩ ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች የተወሰኑቱ የታሰሩት “ለኦነግ ስንቅ ሰጥታችኋል” በሚል ምክንያት እንደሆነ መስማታቸውንም አክለዋል። የከተማይቱ ነዋሪዎች እታሰራለሁ በሚል ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“እስካሁን ምንም ግጭት የለም ግን ፍርሃት አለ። ሰው እንደፈለገ መንቀሳቀስ አይችልም። ሁለት ሆነው አብሮ መቆም፣ መሄድ አይችልም። በየቦታው ፍተሻ ነው። አሁን ከተማ ውስጥ ያለው በጣም የሚያስፈራ ድባብ ነው” ሲሉ የከተማይቱ ነዋሪ በሻምቡ ያለውን ሁኔታ ገልጸውታል። “ከ12 ሰዓት በኋላ መንገድ ላይ የተገኘ ሁሉ ይደበደባል፤ ይታሰራል። በጣም አስፈሪ እና አስጊ ነው” ብለዋል።

በሻምቡ ትላንት በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ከዚህ ቀደም ለሶስት ጊዜያት ለእስር የታደረገችው ጫልቱ ታከለ እንደምትገኝበት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የቤተሰብ አባል ለDW ተናግረዋል። ከእርሷ ጋር ሶስት የጎረቤት እና የሰፈር ሰዎች መታሰራቸውንም ገልጸዋል።

ጫልቱ ትላንት ጠዋት በኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተወስዳ ከሰዓታት በኋላ ብትመለስም በድጋሚ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ መብራት ኃይል በተሰኘው የከተማይቱ ክፍል ከሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ተይዛ መታሰሯን አብራርተዋል። በቁጥጥር ስር ያዋሏት የክልሉ ፖሊሶች “ከኮማንድ ፖስት ነው የመጣነው” ከማለት ውጪ ለእስር ያበቃት ምክንያት ምን እንደሆነ አለመግለጻቸውንም አስረድተዋል።

ፖሊሶቹ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልያዙ እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ታጅባ ወደ ሆሩ ጉድሩ ፖሊስ መምሪያ እንድትወሰድ አድርገዋል ብለዋል። ስንቅ ለማቀበል ወደ ፖሊስ መምሪያው ያመሩት ቤተሰቦቿ ትላንት ማምሻውን እና ዛሬ ጠዋት እንዳነጋገሯት እኚሁ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።

ጫልቱ ከዚህ ቀደም በ1997 ዓ. ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ተይዛ ለአንድ ዓመት ታስራ ተፈትታለች። በ2000 ዓ. ም. በኦነግ አባልነት ተጠርጥራ በድጋሚ ከተያዘች በኋላ 12 ዓመት ተፈርዶባታል። ስምንት ዓመት ከአንድ ወር ገደማ ታስራ በ2009 ዓ.ም. የተፈታችው ጫልቱ ብዙም ሳትቆይ እንደገና ወደ እስር ቤት እንድትመለስ ተደርጓል። ለሶስተኛ ጊዜ ለ11 ወራት በእስር የቆየችው ጫልቱ በየካቲት 2010 ዓ. ም. የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ሲለቀቁ እርሷም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆናለች።

ምንጭ:- የጀርመን ድምፅ ራድዮ
@tsegabwolde @tikvahethiopia