TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.3K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
⚫️ #ኢትዮጵያ ⚫️ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ምን ያልተፈጸም ፤ ምንስ ያልተደረገ ግፍ አለ ? እጅግ በጣም ሚያስደነግጠው እንዲሁም ፍጹም ከሰውነት ተራ እየተወጣ መሆኑን የሚያሳየው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ልክ ጀግንነት ፣ በጎ ተግባር፣ ፍቅርን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ይመስል ግፍና ጭካኔያቸውን በቪድዮ ማስረጃ እራሳቸው ቀርጸው ለትውልድ እያስቀመጡ መሆናቸው ነው። በእርግጥም እንዲህ እየቀረጹ ማስቀመጣቸው…
የእውነት ያለቀስነው መቼ ነው ?

አሁን ላይ ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ምን ያህል ግፍ ምን ያህል ጭካኔ ሀገራችን ውስጥ እንደተፈጸመ መናገር መቼም ለቀባሪው ማርዳት ነው።

ግን ግን እውነት አብረን ያለቀስንበት ቀን መቼ ነው ? ትዝ የሚለውስ አለ ?

አንዱ በሀዘን ተሰብሮ ሲያለቅስ አንዱ ይስቃል  ይደሰታል ፤ አንዱ ሲደሰት አንዱ ያለቅሳል። ሁሉንም አንድ የሚያደርገው የሰብዓዊነት ስሜትም እየታየ ጠፍቷል ፤ ሞቶ አፈር ለብሷል።

ለማዘን ቅድሚያ ጥያቄው " ማነው ? የትኛው ወገን ነው ? " ብሎ መጠየቅ ተለማምደነዋል። " የኔ " የምንለው ሲሆን ማልቀስ " የሌላው ነው " ብለን ስናስብ ምንም እንዳልተፈጠረ ማለፍ ከዛም ከፍ ሲል ግፉን ኖርማል ለማድረግ መሮጥ ስራችን ሆኗል።

ሌላው ይቅር ግፍና መጥፎ ተግባር ማውገዝ እንኳን ሂሳብ ተሰልቶ ጥቅምና ጉዳቱ ታይቶ፣ ጩኸቱንና የህዝቡን ቁጣ ተመልክቶ ሆኗል።

ከምንም በላይ የሚስፈራው ጭካኔና ግፍ ለሚፈጽሙ ግለሰቦች ያውም ከነማስረስረጃቸው ለሚታዩ ሰዎች ጥብቅና መቆም ለነሱ መከራከር ልምድ እየሆነ መምጣቱ ነው።

" እባካችሁ ነገሩ በደንብ ይጣራ " ማለት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ሰው የግፍ ፈጻሚዎቹ ማንነት የኔ ወገን ነው ብሎ ካሰበ " በፍጹም እንዲህ አያደርጉም ፤ የተፈጠሩበት ተፈጥሮና ስነልቦና አይፈቅድም " ብሎ ድምዳሜ በመስጠት ሌላ ግፍ መፈጸም ተለምዷል።

በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ... በሌሎችም ክልሎች በመንግሥት ታጣቂዎች፣ መንግሥትን እንፋለማለን ብለው በወጡ ታጣቂዎች ፣ ፓለቲከኞች በሚሰሩት ጥላቻ የተመረዙ ከማህበረሰቡ በወጡ ሰዎች ለማየት የሚከብድ ብዙ ግፍ ተሰርቶ ያውም በቪድዮ ተቀርጾ ታይቷል ዛሬም እዚሁ መንደር አለ።

ድርጊቶቹ ይፋ ሲወጡ አብሮ በጋራ ከማዘን ፍትህን ከመጠየቀ ይልቅ የፈጻሚዎቹ ደጋፊ ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች በዘመቻ ነገሩን ለማራከስ እና እንዳልተፈጸመ ለማሳየት የሚሄዱበት ርቀት እውን ነገ ለወጥ ይመጣል ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

በሌላኛው ጎራ በንጹህ ሰው ደም ጥቅም ያስገኝልኛል ያለውን ፖለቲካ ይጫወታል። ከበፊትም እጠላዋለሁ የሚለውን አካል መርጦ ሌላ እልቂት ይቀሰቅሳል።

በዚህም መሃል በርካቶች እንደወጡ ቀርተው ፍትህ አላገኙም።

ለማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች እና ሰላም ያለበት ከተማ ለሚኖሩ ነገሩ የሁለት ቀን ግፋ ቢል የሶስት ቀን አጀንዳ ሆኖ ያልፋል። ከዛ ሌላ ግፍ ይፈጸማል።

እናት አምጣ የወለደችውን ፤ ለፍታ ያሳደገችውን ልጅ እያሰበች ዘላለም በለቅሶ ትኖራለች። ወዳጅ ዘመድ ግፉን እያሰበ አመለካከቱ ተቀይሮና በመጥፎ ስሜት ተሞልቶ ለሌላው እንዳያዝን ሆኖ ይኖራል።

የስንቱ ቤት በሀዘን ፣ የስንቱ ሰው ልብ በቂምና ቁርሾ ፤ ሳይወድ በግዱ በመጥፎ አመለካከት ተሞልቶ ይሆን ?

ይህ ነገር ማብቃት አለበት። ተስፋ የሚሰጥ ትንሽ ሰብዓዊነት ሊኖር ይገባል። ማንም ይሁን ማን ተጠያቂነት ሊፈጠር፣ ፍትህ ሊሰፍን ይገባል።

እናቶች የሞተው ልጆቻቸውን ባይመልስላቸውም ፍትህ ሲያገኙ ቢያንስ እንባቸው ይታበስ ተስፋቸው ይለመልም ይሆናል።

ፍትህ ሲገኝ ዜጎች በሀገራቸው ተስፋቸው ያብባል።

በምንም አይነት ሁኔታ በግጭት ፣ በጦርነት ሆነ በምንም መንገድ በምድሪቱ ደም አይፈሰስ ፣ ሰው አይበደል ፤ የሰው ደም በፈሰሰ ቁጥር ፤ በደል በተፈጸመ ቁጥር ቂም ጥላቻ፣ አለመተዛዘን እየተወለደ እየተስፋፋ ይመጣል።

ደስታውስ ይቅር እውነት አብረን መቼ ነው በጋራ ያለቀስነው ? ብለን እንጠይቅ። ከልብ እንኮንን፣ ሂሳብ አንስራ ፤ የሰው ደም ላይ ፖለቲካ አንቆምር ፤ ለፍትህ እንታገል ! ካልሆነ የሁላችን እጣ ፋንታ እንደወጡ መቅረት ፍትህ አለማግኘት ይሆናል።

#TikvahEthiopia
#ቲክቫህኢትዮጵያ
#ናውስ

@tikvahethiopia