TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
59.3K photos
1.51K videos
212 files
4.11K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በከባድ መሳሪያ ተመታ።

ሱዳን ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት የንብረት ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ የደረሰው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 22/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ነው።

የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ በኤምባሲው ሕንጻ እና ንብረት ላይ ውድመት ያደረሰ ሲሆን፣ በሰው ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

በካርቱም አል-አማራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት በተለያዩ ኃይሎች ተደጋጋሚ #ጥቃት እና #ዘረፋ እንዳጋጠመው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ዲፕሎማት ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አንደኛው ተፋላሚ ወገን የሆነው በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መድረሱን ገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለጥቃቱ ተቀናቃኙን በጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራውን የሱዳን ጦር ሠራዊትን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፣ በኤምባሲው ላይ በተፈጸመው ጥቃት " በሕንጻው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል " ብሏል።

በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ ለምን እንደተፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን ስለክስተቱ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሐን ኃይሎች በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በዛሬው ዕለት ጠዋት ላይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጨማሪ በዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ በሩሲያ እና በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎችም ላይ ጥቃት መፈጸሙን ቢቢሲ ዲፕሎማቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ፎቶ ፦ ፋይል

@tikvahethiopia