TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
59.3K photos
1.51K videos
212 files
4.11K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኦሮሚያ

" በቤጊ ሁለት ቀበሌዎች ረሃብ ተከስቷል "

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ረሃብ መከሰቱ ተነገረ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና ራሱን " የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጪ " ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲንቀሳቀስባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል በቤጊ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ረሃብ መከሰቱን የምዕራብ ወለጋ ዞን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ " ሸኔ የያዛቸውና ለጥቂት ጊዜያት ያስተዳደራቸው ወረዳዎች ነበሩ።  እነዛ ወረዳዎች ብዙ ችግሮች ገጥሟዋቸዋል " ብለዋል።

ለአብነት ታጣቂ ቡድኑ ሲንቀሳቀስባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች #ረሃብ መከሰቱን ገልጸዋል።

አቶ ሰለሞን ፣ " እስፔሻሊ ጠረፍ ላይ የሚገኙ ቀበሌዎች ተጎድተዋል። በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ተጋባና ሻንታ ቀበሌዎች ረሃብ አለባቸው " ብለዋል።

ረሃብ ተከሰተበት የተባለውን የቤጊ ወረዳ ሁኔታን ሲያስረዱም አቶ ሰለሞን ፣ " መሰረተ ልማት፣ ቀበሌዎች፣ የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በጣም ጉዳት የደረሰበት ወረዳ ነው " ብለዋል።

" ከጤና ጋር በተያያዘ ቢያንስ 45 የሚሆን ጤና ኬላ ወድሟል ወደ አምስት ጤና ጣቢያዎች ተቃጥለዋል " ሲሉ አስታውሰው፣ ወረዳውን ታጣቂ ቡድኑ ሲቆጣጠረው አርሶ አደሩ እንዳያርስ በማዳበሪያ እንዳይጠቀም፣ ማኅበረሰቡ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ ማድረጉን አስረድተዋል።

" ሸኔ አገሪቱን ወደ ድህነት የሚመራ እንጂ ምንም አላማ የሌለው ነው " ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ ታጣቂ ቡድኑ " በቄለም ወለጋና  በቤጊ፣ በቆንዳላ በተለይ ገጠሩን አካባቢ ተቆጣጥሮ ጉዳት አድርሷል። ሰው ገድሏል። ብዙ ንብረቶች በዚህ ታጣቂ ቡድን ወድመዋል " በማለት ተናግረዋል።

ረሃብ የተጋረጠባቸው የሰሊጥ አምራቾች ናቸው ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ፣ " ሸኔ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በሚወስድበት ጊዜ ቀቅሎ እንዲበላ ሲያደርግ ነበር። መብላት ማለት እንደ ምግብ እንዲበላ በማድረግ እንዳያርስበት፣ እንዳይጠቀምበት ማድረግ ነው " ብለዋል።

ነዋሪዎች በበኩላቸው በተከሰተው ረሃብ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸው፣ መንግሥት የምግብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አክለውም፣ በወባ ወረርሽኝም የሰው ሕይወት እያለፈ መሆኑን አስረድተዋል።

በረሃብ የሞተ ሰው እንዳለና እንዴሌለ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አቶ ሰለሞን ፣ " ከረሃብ የተነሳ የሞተ ሰው ሪፓርት አልደረሰኝም። ከምግብ ጋር በተያያዘ ግን የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ሰሞኑን 400 ኩንታል ዱቄት አድርሷል። እርዳታ ግን አሁንም ያስፈልጋል " ብለዋል።

ከረሃብ ባሻገርም በዞኑ በሚጉኙ ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ እንደተከሰተ፣ #የሞቱ ሰዎችም እንዳሉ ገልጽው፣ መንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች እርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

መንግሥት " ኦነግ ሸኔ " እያለ የሚጠራውና እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የሚለው ታጣቂ ቡድን ከላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቀረበበት ክስ ዙሪያ ይፋዊ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ተከታትለን እናሳውቃለን።

@tikvahethiopia
#ነዳጅ📈

የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል ሲሉ የነዳጅ ላኪዎች ህብረት መሪ አስጠነቀቁ።

የ23 ነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት የሆነው ኦፔክ+ ዋና ፀሀፊ ሄይታም አል ጋይስ ፤ ለሃይል አቅርቦት ያለው ፍላጎት በመጨመሩ የነደጅ ዋጋ እንዳሻቀበ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ጸሃፊው " በቀን የነዳጅ ፍላጎት ወደ 2.4 ሚሊዮን በርሜል ሲያድግ እየተመለከትን ነው " ብለዋል።

ሁለቱ ዋነኛ የነዳጅ አምራችና ' ኦፔክ+ ' አባል የሆኑት ሳዑዲና ሩሲያ የወሰኑት ውሳኔ በዚህ ዓመት መጨረሻ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት ያስከትላል ሲል ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።

" ይህ ሁለት ሉአላዊ ሀገራት ሳዑዲ አረቢያ እና ሩስያ በፍቃደኝነት የወሰኑት ነው። ይህ ውሳኔ እርግጠኛ ልንሆንበት በማንችልበት ሁኔታ ምክንያት የተደረገ ጥንቃቄ ወይም ቅድመ ዝግጅት ብለን ልንገልጸው እንችላል " ሲሉ የኦፔክ+ ዋና ጸሃፊ ተናግረዋል።

ሰሞኑን በምርት እጥረት ምክንያት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 95 ዶላርን አልፎ የነበረ ሲሆን ዋጋው 100 ዶላርን ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ይህ የዋጋ ለውጥ በሚቀጥሉት 10 ወራት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ሊያሻቅብ እንደሚችልና በወሳኝ የኢኮኖሚ መስኮች ያለው የዋጋ ግሽበት ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ምክንያት ይሆናል የሚል ስጋትን ማጫሩን #ቢቢሲ ዘግቧል።

@tikvahethiopia
" እስካሁን ውጤት አልተገለፀም " - የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የ2015 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት እስካሁን #አልተገለፀም ሲል አሳውቋል።

ተፈታኞችና መላው የትምህርት ማህበረሰብ #በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በፀጥታና ሌሎች ምክንያቶች ፈተና ሳይወስዱ የቆዩ ተማሪዎች ፈተናቸውን መውሰዳቸው ይታወቃል።

የነዚህ ተማሪዎችን ፈተና ውጤት በሐምሌ 2015 ዓ.ም ከተፈተኑ ተማሪዎች ጋር አብሮ ይፋ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም " እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ውጤቱ ይፋ ሊደረግ እንደሚችል " የአገልግሎቱ ከፍተኛ ኃላፊ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

@tikvahethiopia
" በኢሬቻ በዓል ላይ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ  ፁህፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ ነው " - ግብረ ኃይሉ

እጅግ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የሚገኝባቸው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታ ኃይሎች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸው ተገለጸ።

ይህን የገለፀው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ነው።

በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ ይከናወናል ብሏል።

በአዲስ አበባ ለሚከበረው በዓል ለወንጀል መከላከል ተግባር ልዩ ትኩረት መሰጠቱ የተገለፀ ሲሆን አብዛኛውን የሰው ኃይል  በወንጀል መከላከል ስራ ላይ እንዲሰማራ መደረጉ ተነግሯል።

በኢሬቻ በዓል ላይ ምን ተከልክሏል ?

- ከባህላዊ አከባበሩ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት መፈፀም አይቻልም።

- ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ  ፁህፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ ነው።

- ባህላዊ ሥርዓቱን ሊያውክ የሚችል ማኛውም ተግባር ማከናወን ፍፁም የተከለከለ ነው።

ግብረ ኃይሉ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች #ፍተሻ መኖሩን ተገንዘበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፏል።

ህብረተሰቡ ማንኛውም አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ መስጠት ይቻላል ተብሏል።

@tikvahethiopia
#Amhara

#እቅድ፦ 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ

#እስካሁን_የተመዘገቡት ፦ 2,937,556 ተማሪዎች

በአማራ ክልል ለዘንድሮ ዓመት ትምህርት ይመዘገባሉ ተብለው ከታሰቡት 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገብ የተቻለው 2,937,556 ተማሪዎችን እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሳውቋል።

ይህ ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ሲሆን ካለፉት ዓመታት ሲነፃፀር እቅዱ አጥጋቢ እንዳልሆነ አመልክቷል።

የሚጠበቀውን ያህል ተማሪዎች እንዳይመዘገቡ ከሆነበት ምክንያቶች አንዱ በክልሉ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች ያለው የትጥቅ ግጭት መሆኑ ተነግሯል።

አንዳንድ ዞኖች እስካሁን ጭራሽ ምዝገባም ያልጀመሩ ሲሆን እነዚህም የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ፣ ምስራቅ ጎጃም ፣ ምዕራብ ጎጃም ደብረማርቆስ ፣ ሰሜን ጎጃም እንደሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተፅእኖ አሳድሮብናል ያለው ትምህርት ቢሮ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የተማሪ ምዝገባ መከናወኑን አመልክቷል። አንዳንድ ዞኖችም የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግበዋል ሲል አክሏል።

አሁንም የምዝገባ ቀኑ ያልተገደበ ሲሆን ዞኖች ጎን ለጎን የመማር ማስተማር ስራውን እና ምዝገባውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ ነው ማለቱን ቪኦኤ ዘገቧል።

ፎቶ ፦ ፋይል

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Tigray #Update

ከጥቅምት 3 እስከ 5/2016 ዓ.ም ተፈፃሚ የሚሆነው የትግራይ የሃዘን ቀን ማሰፈፀምያ መመሪያ ይፋ ሆነ።

ከመስከረም 21/2016 ዓ/ም ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆንና የጊዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕረዚደንት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ፊርማ ያረፈበት 18 አንቀፆችን የያዘ የትግራይ የሃዘንና መርዶ " መመሪያ ቁጥር 022016 " ምን ይላል ? 

የመርዶና የሃዘን ስነ-ሰርአቱ ጥቅምት 2 ታውጆ ከጥቅምት 3 እስከ 5 የሃዘን ቀናት ይሆናል። ጥቅምት 6 /2016 ዓ.ም የሃዘን ቀን ስነ-ሰርአቱ ያበቃል።

ከጥቅምት 3 እስከ 5 /2016 ዓ.ም በሚኖሩ የሃዘን ቀናት በመመሪያ የተከለከሉና በህግ የሚያስቀጡ ዝርዝር ተግባራት ተቀምጠዋል።

1ኛ. ስፓርታዊ ጨወታዎች ጨምሮ ድምፅ የሚፈጥር ንግዳዊና ንግዳዊ ያልሆነ ተግባር የተከለከለ ነው።  

2ኛ. ቀንና ማታ በሙዚቃ በመታጀብ የሚሰሩ መጠጥ ቤቶች ፣ የቡናና ተመሳሳይ የሽያጭ አገልግሎት የሚሰጡ ዝግ ይሆናሉ።

3ኛ. ሰርግ ፣ የህፃናት ክርስትና ፣ ልደትና የመሳሰሉ ድምፅ የሚፈጥሩ ተግባራት አይፈቀዱም። 

4ኛ. ጥይት መተኮስ የተከለከለ ነው። 

በትግራይ ደረጃ የሚከናወነው የሃዘን ቀን ስነ-ሰርአት ተጠናቆ ተለዋጭ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ ፍፁም የተከለከሉና በህግ የሚያስቀጡ ተግባራት የሚከተሉት ናቸው። 

1ኛ. የተሰዋ ታጋይ አስከሬን ካረፈበት ቦታ ማንሳትና ማዘዋወር የተከለከለ ነው።

2ኛ. የተሰዋ ታጋይ ሃወልት መገንባት ወይ ደግሞ ያረፈበት መቃብር ማሻሻልና መለወጥ የተከለከለ ነው።

3ኛ. የተሰዋ ታጋይ አስከሬን ያረፈበት ቦታ መጠቆምና ከቦታው ለማንሳት ጥቅም መጠየቅና መቀበል የተከለከለ ነው።

4ኛ. የተሰዋ ቤተሰብ ክብርና መንፈስ የሚጎዳ ፣ የሚያደበዝዝ ተግባር መፈፀም የተከለከለ ነው።

5ኛ. አገልግሎት ሰጪ የግል ድርጅቶች ሳይጨምር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት #ዝግ ይሆናሉ።

በመመሪያ የተጠቀሱ ህጎች የማያከብሩና የሚጥሱ ግለሰቦችና ተቋማት ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ቅጣት የተቀመጠ ሲሆን ቅጣቱን ለማስፈፀም የፓሊስና የፍትህ አካላት ያካተተ 8 ኣባላት ያሉት ግብረ ሃይል በወረዳና ቀበሌ ደረጃ መቋቋሙ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።

#TikvahEthiopiaMekelle

@tikvahethiopia
አሜሪካ የDV-2025 አመልካቾችን መቀበል ጀመረች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊውን የዲይቨርሲቲ ቪዛ (#ዲቪ) ፕሮግራም / " ግሪን ካርድ ሎተሪ " በመባል የሚታወቀውን በአሜሪካ ለመኖር እና ለመስራት ለሚፈልጉ አመልካቾች ዛሬ ክፍት አድርጓል።

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ መርሃ ግብሩ ዛሬ ሩቡዕ ጥቅምት 4 ተጀምሮ ማክሰኞ ህዳር 7 ቀን 2023 ይጠናቀቃል።

አሜሪካ አሁን ባለው ፕሮግራም 55000 ለሚደርሱ የውጭ ዜጎች የግሪን ካርድ እድል ትሰጣለች።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲቪ ፕሮግራም ለመመዝገብ / ለማመልከት ምንም አይነት ክፍያ እንደሌለው አሳውቋል።

ነገር ግን ወደፊት ለቃለ መጠይቅ ቀጠሮ የተያዙ ተመራጮች መደበኛ የቪዛ ማመልከቻ ከማቅረባቸው በፊት የቪዛ ማመልከቻ ክፍያ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። እነዚህ ተመራጮች በቆንስላ ኦፊሰር አማካኝነት ለቪዛ ብቁ መሆን አለመሆናቸውን የሚወሰንላቸው ናቸው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዲቪ ለመሙላት ብቁ ከሆኑ በርካታ ሀገራት 55,000 አመልካቾች በዘፈቀደ በውስጥ ስርዓት ይመረጣሉ።

አስፈላጊ #መመሪያዎችን ፣ መስፈርቶችን እንዲሁም ለማመልከት ይህን ትክክለኛ ድረገፅ ይከተሉ፦ https://dvprogram.state.gov/

አመልካቾች ዲቪ ለማመልከት #ክፍያ_የማያስፈልግ ስለሆነ ከአጨባርባሪዎች እንዲጠነቀቁ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia
" የሚቀበለንን አጥተናል " - የቀድሞ የደቡብ ክልል ሰራተኞች

ከቀድሞዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወደተለያዩ ቦታዎች የተበተኑ የመንግስት ሰራተኞች የሚቀበለን አጣን እያሉ ነዉ።

የደቡብ ክልል ለሁለተኛ ጊዜ  ወደሁለት ማለትም የደቡብ ኢትዮጵያና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተብሎ መከፈሉን ተከትሎ በቀድሞዉ የደቡብ ክልል ስር የነበሩ ሰራተኞች ወደአራቱ ክልሎች መደልደላቸዉ ይታወሳል።

ይሁንና ከአራቱ ክልሎች መካከል በሲዳማና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የተመደቡ ሰራተኞች ክልሉ አልተቀበለንም ሲሉ ቅሬታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት የሲዳማ ክልል በሲዳምኛ ቋንቋ የመጻፍና የማንበብ ክሂል ሲጠይቅ የደቡብ ምእራብ ክልል በበኩሉ የምፈልገዉን የሰራተኛ መጠን ይዤ ሄጃለሁ አሁን ላይ የምፈልገዉ ጽዳትና የመላላክ ስራ ነዉ በማለት የተመደቡትን ሰራተኞች መቀበል አልቻሉም።

ይህን ጥያቄ ይዘዉ ካሁን በፊት ወደተቋቋመዉ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ቢሄዱም ምላሽ የሚሰጣቸዉ አካል ያጡት የቀድሞ ደቡብ ኢትዮጰያ ሰራተኞች የሚመለከተዉ አካል አቤቱታቸውን እንዲሰማቸዉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የሀዋሳ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ምላሽ ለማግኘት ያደረገዉ ጥረት አልተሳካም። ምላሽ እንዳገኘን እንልካለን።

@tikvahethiopia
የሰቆጣና አካባቢው የሚፈፀመው ዝርፊያ !

• " ስርቆቱ በዚህ ከቀጠለ ለህበረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማድረስ እንቸገራለን " - የሰቆጣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ

• " የመብራት ሃይል ገመድና የውሃ ቧንቧዎችን ሲሰርቁ የተያዙ  5 ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል " - የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መመሪያ

• " የተዘረፈ ንብረት ስለመኖሩ አላውቅም " - ፖሊስ መምሪያ

ሰቆጣ ከተማ እና አካባቢው ላይ ማንነታቸው አልታወቁም በተባሉ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ መስመሮች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ተብሏል።

ይህን ያለው የሰቆጣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ነው።

8 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች ተሰርቀው ተወስደዋል ያለው ማዕከሉ በብር ሲገመት 8 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል።

ማዕከሉ ፤ በተለያዩ ግዚያት የተዘረፉትን መሰረተ ልማቶች ለሚመለከተው የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ቢያሳውቅም አጥፊዎችን አሳዶ በመያዝ ረገድ መፍትሄ አልተገኘም ብሏል።

ተዘርፈው ከተወሰዱት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ፋጥዝጊ ክሬችር፣ እርሻ ምርምር  የዝቋላ መገንጠያ፣ ባር ኪዳነምህረትና ቄቫ በተባሉ አከባቢዎች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ይገኙበታል።

ወንጀለኞች ተይዘው ለህግና ለፍርድ ካልቀረቡና የስርቆት ዘረፋ በዚሁ ሂደት ከቀጠለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድርግ እንደሚቸገርም አገልግሎቱ አሳውቋል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መመሪያ በበኩሉ የመብራት ሃይል ገመድና የውሃ ቧንቧዎችን ሲሰርቁ የተያዙ  5 ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን ገልጿል።

የስርቆት ድርጊቱ  ሊቆምና ሊቀነስ ባለመቻሉ የፀጥታ መዋቅሩ ይበለጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚጠይቅ ወቅት ነው ብሏል።

እየወደሙ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ለማስቆምና ዘረፋን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግም አመልክቷል።

ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የንብረቱ ባለቤት ሆኖ ካልጠበቀ ተፈላጊውን አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል አስገንዝቧል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ደግሞ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ስለመዘረፉ ምንም አይነት መረጃ እንዳልደረሰውና " የተዘረፈ ንብረት ስለመኖሩ አላውቅም " ብሏል።

በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች  ህዝብን የሚጎዱ በመሆናቸው ከፖሊስ ኦፊሰሮች ጋር በመነጋገር በተቻለ መጠን ጥበቃ ይደረጋል ሲል ገልጿል።

ማንኛውም ቦታ ላይ ፖሊስ ሊመደብ ስለማይቻል በመሰረተ ልማቶች ላይ ማህበረሰቡ የራሱን ጥበቃ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል።

መረጃው ከዋግኽምራ ኮሚኒኬሽን የተገኘ ነው።

@tikvahethiopia