TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
59.3K photos
1.51K videos
212 files
4.11K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ባህር ዳር🔝

በባህር ዳር የተደረገው የጎዳና ላይ እና ከትራፊክ ፍሰት የጸዱ መንገዶች ቀን ሩጫ ተጠናቀቀ። በሩጫዉ ከአትሌቶች አስረስ ጓዴ ከአዉስኮድ ይኸይስ አበባዉ ከደባርቅ ዋልያ ትግስቱ ምህረቱ ከአዉስኮድ አትሌቲክስ ክለብ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት አሸንፈዋል፡፡ በሴት አትሌቶች ደግሞ ቸርነት ምስጋናዉ ከሰሜን ጎንደር፣ ወርቅነሽ ስንሻዉ ከባሕር ዳር እና መሰረት ሙጨ ከመሸንቲ ድል አድርገዋል። ከተሳታፊዎች አየለ ሙጨ ይታየዉ፣ ፈንታ አሊ ሁሴን ተከታትለዉ ገብተዋል። የሜዳሊያና ገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከተሳታፊዎች አብመድ ያነጋገራቸዉ ግለሰቦች እንደገለጹት ሩጫዉ ለጤንነት ጠቃሚ ነዉ ይበል የሚያስብል ነዉ። ወደፊትም መቀጠል አለበት የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። አብመድ እንደዘገበው በመርሃ ግብሩ ጥርን በባሕር ዳር በሩጫ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና ሰርከስ ታጅቦ በማያያዝ መገባደጃዉን አግኝቷል።

ምንጭ፦ አብመድ
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#update የቀድሞ የህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት አፈጉባኤ የአምባሳደር ዳዊት ዮሃንስ የቀብር ስነስርዓት በዛሬው ዕለት ይፈፀማል። የአምባሳደሩ አስከሬን ቦሌ አለምአቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤው #ኬርያ_ኢብራሄምን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው አቀባበል አድርገዋል:: አምባሳደር ዳዊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከህዳር 1987 ዓ/ም ጀምሮ ለ2 የተለያዩ ጊዜያት በአፈ ጉባዔነት አገልግለዋል። አምባሳደር ዳዊት ከፖርላማ አፈጉባኤነት በተጨማሪ በዲፕሎማሲውም መስክም ሀገራቸውን አገልግለዋል።

via epa
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#update ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ የጊዴቦ ግድብ ስራ ፕሮጀክትን ዛሬ ጥር 26 ቀን 2011 መረቁ:: በዛሬው ምረቃ ስነስርዓት ላይም የኦሮምያ ክልል ርእሰ መስተዳድር #ለማ_መገርሳና የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር #ሚሊዮ_ማቲዎስ ተገኝተዋል።

#PMOEthiopia
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#update ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ #ዝናሽ_ታያቸው በምዕራብ ጉጂ ዞን ሱሮ በርጉዳ ወረዳ ለሚገነባ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የመሰረተ ድጋይ አስቀመጡ፡፡ የሚገነባው የሁለተኛ ድርጅት ትምህርት ቤት ሲጠናቀቀ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአካባቢያቸው መከታተል እንደሚያስችላቸው ተነግሯል፡፡

via fbc
@tsegabwolde @tikvahethiopia
የሀሰት ዋጋው‼️

እሳት፣ ውሃ፣ እውነትና ሃሰት የሚባሉ ጓደኛሞች ነበሩ። በዚህ ጓደኝነታቸው ግን ሃሰት ብዙም አልተደሰተም። ጥምረቱም ደስተኛ አላደረገውም። ስለዚህም #አንድነታቸውን ማበላሸት ፈልጎ እንዲህ አለ፤ «ለምን ወደ አንድ ስፍራ ተጉዘን እያንዳንዳችን የራሳችንን ግዛት አንመሰርትም? ስለዚህ ተነስተን አብረን እንጓዝ።»

ሁሉም በሃሳቡ ተስማምተው ሲሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ #ሀሰት ወደ #ውሃ ጠጋ ብሎ «እሳት ሳሩን፣ ደኑንና ቁጥቋጦውን የሚያቃጥል ቀንደኛ ጠላታችን ስለሆነ ለምንድነው ከእርሱ ጋር ግዛት ፍለጋ የምንሄደው?» አለው። ውሃም «ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?» ሲል መልሶ ጠየቀው።

ሃሰትም ቀበል አድርጎ «ልንገድለው እንደሚገባ ግልፅ ነው፤ እሳትን የማጥፋት ብቸኛ ኃይል ያለህ ደግሞ አንተ ነህ። እናም ቁጭ ሲል ጠብቀህ እላዩ ላይ ራስህን በመርጨት አጥፋው» አለው። ውሃም «ራሴን መሬቱ ላይ ከረጨሁ ተመልሼ ውሃ መሆን አልችልም» አለ። ሀሰትም «ችግር የለውም፤ ተረጭተህ እንዳትበታተን የተወሰኑ ድንጋዮች በዙሪያህ አኖርና በኋላ እሰበስብሃለሁ» አለው።

በዚህ ጊዜ የተሸረበበትን ተንኮል ያልጠረጠረው እሳት ቁጭ ሲል፤ ውሃው አንድ ጊዜ በላዩ ላይ ሲረጭ ሃሰት ድንጋዮች ዙሪያውን አድርጎ ውሃውን ከሰበሰበውና እሳትን ካስወገዱ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃሰት ውሃውን «ለምን እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ቁጭ ብለህ በተፈጥሮ ውበት አትዝናናም?» አለው። ውሃም አፋፉ ላይ ቁጭ ሲል ሃሰት ቀስ ብሎ ተነስቶ ውሃ የተቀመጠባቸውን ድንጋዮች ከስሩ ሲለቅማቸው ውሃው በዚያው ተበታትኖ ጠፋ።

በመጨረሻም ሃሰት እውነትን ማጥፋት ነበረበትና ወደ አንድ ትልቅ ተራራ በተቃረቡ ጊዜ ሃሰት እውነትን ከተራራው ግርጌ ቁጭ በል ብሎት ከተራራው አናት ላይ ትልቅ አለት ቁልቁል በመልቀቅ እውነትን ሊጨፈልቀው ሲል እውነት ቀልጠፍ ብሎ ማምለጥ በመቻሉ አለቱ ተንከባሎ ሲፈረካከስ ከውስጡ አልማዝ፣ ወርቅና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት ወጡ። ሃሰትም የእውነትን አስከሬን ሊመለከት በመጣ ጊዜ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ድንጋዮች አየ። እናም «እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ?» ብሎ ጠየቀ። እውነትም «አለቱ እላዬ ላይ ሲወድቅ እነዚህ ማዕድናት ወጡ» ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ሃሰት «አሁን ደግሞ እኔ ከተራራው ግርጌ ልቀመጥና አንተ አለቱን በላዬ ላይ ልቀቅብኝ» አለው። እናም እውነት ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ትልቅ አለት ወደታች በለቀቀ ጊዜ አለቱ የሃሰት አናት ላይ አርፎ ሃሰትን ጨፈላልቆ ገደለው። ይህ የሚያሳየው ሀሰት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልና እውነት ፈተና ቢገጥመውም በመጨረሻ አሸናፊ እንደሚሆን ነው። በተለይ አሁን በሀገራችን የሀሰት መረጃ እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር ስናነጻጽረው ትልቅ መልዕክት ይሰጠናል።
የማገናዘብና ትክክለኛውን መረጃ አውቆ ወደ ተግባር መግባት ላይ ብዙዎች ችግር አለባቸው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ የሀሰት ወሬ ነው። ይህንን አድርግና ይህንን ታገኛለህ የሚለው የተሳሳተ መስመር ብዙዎችን ባልተገባ መንገድ እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። ሰው በሰው ላይ በክፋት አስነስቷል። እውነቱ እንደ እውነትነቱ መጨረሻ ማሸነፉን የሚዘነጋ ሰው አይጠፋም።

በእርግጥ በሌሎች ስህተት ውስጥ አለመሳተፍ ዋጋ ይኖረው ይሆናል። ልክ እንደ እሳት ማለት ነው። ነገር ግን እንደ በሀሰት ዝም ብሎ ሰዎችን ማባላትና ማገዳደል መጨረሻው ራስን ለጉዳት ይዳርጋል፡፡ የህግ ተጠያቂነትም ያስከትላል። በአገሪቱ ውስጥ እሳትን የሆኑ፣ ሀሰትን የሆኑ እንዲሁም እውነትን የሆኑ ሰዎች አሉ።

እሳትን የሆኑት የሚደረገውን የማያውቁ የራሳቸውን አለም ብቻ የሚኖሩ ናቸው። ሀሰትን የሆኑት ደግሞ የሰዎች ሰላም ማጣትና መባላት የሚያስደስታቸው፤ ሁሉ ነገር የእኔ ብቻ የሚሉ፤ ‹‹እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ ናቸው። እውነትን የሆኑት ግን ለአንዲት አገር ለውጥ የቆሙና የአገር መለወጥ የእኔ ለውጥ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።

በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ ርዕዮተ አለምና፣ የተለያየ የትግል ስልት ይኖራል። ሆኖም አንድ ነገር ላይ ግን መግባባት ያስፈልጋል። የሁሉም ጥረት እውነትን ለመገንባት መስራት መሆን አለበት። ምናልባት አንዳንዶቹ ይህ እውነት ተግባራዊ ሆኖ ላያዩት ይችላሉ። ግን አሻራቸው ይኖርበታል። ለቀጣይ ትውልድም መልካም ታሪክ ማስተላለፍ ይችላሉ። በእውነት ለመኖርና ሃገርን ለመገንባት እውነትን መስራት ነው የሚያስፈልገው።

«ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ መጀመሪያ አንተው ራስህ ሁነው» እንዲል ማኅተመ ጋንዲ፤ ለለውጥ በቆረጡ፣ መለወጥ እንችላለን ብለውም በሚያስቡ፣ ከዕለት ጉዳይ አልፈው ታላቁን ሥዕል ለማየት በሚችሉ ሰዎች እውነትን ገንብቶ አገርን በለውጥ ጎዳና ውስጥ ለማስኬድ መጣር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ስለ እውነት ሁሉም በእኩል ደረጃ፣ አቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት እና ሥልጣን መሟገትና መስራት አለበት። ምክንያቱም ሀሰተኞች ለራሳቸውም ሆነ ለአገር አይጠቅሙም፤ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው በእውነት መረታት ነው፡፡

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን
@tsegabwolde @tikvahethiopia