TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
በአውሮፕላኑ የአደጋ ስፍራ በየዕለቱ እየተገኙ የሚያለቅሱት እናት👆

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር በተያያዘ በስፋት ከተሰራጩትና ለአደጋው ሰለባዎች መሪር ሃዘናቸውን ከሚገልፁ ፎቶግራፎች መካከል የአዛውንቷ የወይዘሮ #ሙሉነሽ_በጂጋ ፎቶ አንዱ ነው።

ከዚህ አንፃር የወይዘሮ ሙሉነሽ ታሪክ የተለየ የሚሆነው ደግሞ በአደጋው የሞተ ዘመድም ሆነ በቅርብ የሚያውቁት ሰው ሳይኖር በሰውነታቸው ብቻ ስለደረሰው አደጋ አዘውትረው ማዘናቸው ነው።

አዛውንቷ ወይዘሮ ሙሉነሽ ነዋሪነታቸው በመጥፎ ዕጣ የ157 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው አውሮፕላን በተከሰከሰበት ስፍራ ሲሆን፤ በተመለከቱት አሰቃቂ ክስተት ሳቢያ ከዚያች ዕለት በኋላ እጅጉን አዝነው እንቅልፍ አጥተዋል። እንባቸውንም በአደጋው ለተቀጠፉት ለማያውቋቸው ሰዎች እያፈሰሱ ቀናት ተቆጥረዋል።

የቱሉ ፈራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እኚህ እናት፤ ቤታቸውም አደጋው ከደረሰበት ሁለት ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ቢኖረውም ከአደጋው ቀን አንስቶ አንድም ቀን ከቦታው ርቀው አያውቁም። "እስካሁን ደጋግሜ ከአደጋው ቦታ ሄጄ ባለቅስም ሃዘኔ አልወጣልኝም" ይላሉ።

አሁንም በየቀኑ ወደ ስፍራው ከሚመጡ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሃዘናቸውን ይገልፃሉ። "የሃገሪቷ ሁኔታ ነው የተበላሸው፤ ሰዎች ባህላቸውንና ወጋቸውን በመርሳታቸው የዚህ ሁሉ ሰው ደም ፈሰሰ" በማለት ጉዳዩን ከፈጣሪ ቁጣ ጋር ያያይዙታል።

"ከዚህ በፊት በአያት ቅድመ አያቶቻችን ዘመን አይተንም ሰምተንም የማናቀውን ነገር በእኛ ቀዬ ሲፈጠር በጣም አስደነገጠኝ፤ ይህም ነው ቀን ከሌሊት እንዳለቅስ ያደረገኝ" ይላሉ ወይዘሮ ሙሉነሽ

እኚህ እናት እንዲህ በሃዘን የሚንገበገቡት ለኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ሳይሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ ለነበሩት የሰው ልጆች ነው። "የሰው ልጅ ኢትዮጵያ ሃገራችን መጥቶ ተቃጠለ። ደማቸው ባዶ ሜዳ ላይ መፍሰሱን ሳስብ ሆዴ ይረበሻል። በዕለቱ ስለተከሰከሰው የሰው አጥንትና ስለፈሰሰው ደም አልቅሼ ሊወጣልኝ አልቻለም" ሲሉ የሃዘናቸውን ጥልቀት ይናገራሉ።

አደጋው ከደረሰ በኋላ በስፍራው ስለተመለከቱት ነገርም ሲያስታውሱ፤ የአውሮፕላኑ አካል የተበተነ ወረቀት እንጂ የሰው ልጅ በውስጡ የያዘ አይመስልም ነበር። "ታዲያ ይሄ እንዴት ለእኔ እረፍት ይሰጠኛል? የእነርሱ ደም ነው የሚያቃጥለኝ" ይላሉ ወይዘሮ ሙሉነሽ

በተለይ ደግሞ አደጋ በልጆቻቸው ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮስ ብለው ሲያስቡ ሃዘናቸው የሚብሰው ወ/ሮ ሙሉነሽ "እኛም ልጆች አሉን፤ ልጆቻችንም በአየር ይበራሉ። ታዲያ ከእነዚህ መካከል የእኛ ልጆች ቢኖሩስ ብዬ አስባለሁ።"

ወይዘሮ ሙሉነሽ በየዕለቱ አደጋው የደረሰበት ቦታ ይሄዳሉ። "አንድም ቀን ቀርቼ አላውቅም።" በየአጋጣሚውም እርሙን ለማውጣት ከሚመጣው ሰው ሁሉ ጋር ስለሞቱት ሰዎች ያለቅሳሉ። "ቤትም ስገባ ያ የፈሰሰው የሰው ደም ነው ትዝ የሚለኝ፤ ምግብም አስጠልቶኝ ቡናው እራሱ ቡና አይመስለኝም" ይላሉ።

ይህ አደጋ በወይዘሮ ሙሉነሽ ላይ የተለየ ጥልቅ ሀዘንን ፈጥሮባቸዋል። ከዚህ በፊት በቅርብ የሚያውቋቸውና ከቤተሰባቸው አባላት መካከልም የተለያዩ ሰዎች በሞት ተለይተዋቸዋል። ነገር ግን ይህን ያህል ሃዘን ውስጥ ገብተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉነሽ ይህ ክስተት ለእርሳቸው የተለየ ነው።

ወይዘሮ ሙሉነሽ ይህንን ሃዘናቸውን ልክ እንደ ቤተሰብ ለመግለፅ ባላቸው አቅም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች ኃይማኖታቸው በሚያዘው መሠረት የተዝካር ሥነ-ሥርዓት ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ይናገራሉ።

ምንጭ:- BBC አማርኛ
@tsegabwolde @tikvahethiopia