TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኢትዮጵያ

የኩላሊት እጥበት ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ በሳምንት 3 ጊዜ እጥበት የሚያደርጉ ሕሙማን ከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን፣ የኩላሊት ሕክምና እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል።

ከሰሞኑም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ፤ " መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉም የሕክምና ተቋማት የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል " ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት አንድ ታካሚ የኩላሊት እጥበት ለአንድ ጊዜ ሲያደርግ ይፈጸም የነበረው ክፍያ 2,000 ብር እንደነበር፣ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ሲደረግ አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ተቋማት ከ3,000 እስከ 4,100 ብር እያስከፈሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ለኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ከውጭ ስለሚገቡ፣ የአገልግሎት ክፍያው በእጥፍ መጨመሩንና በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚጠቀም ታካሚ አንድ ጊዜ ብቻ ለማድረግ መገደዱን አክለው ገልጸዋል፡፡

በሞት ከተለዩ ሰዎች ኩላሊት እንዲወሰድ የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ድርጅቱ ጥረት ማድረጉን፣ ጉዳዩም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ በሕግ ማዕቀፍ ሲታገዝ በርካታ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ በቀላሉ እንደሚያደርጉ፣ እስከዚያው ግን ማኅበረበሰቡ ለኩላሊት ሕሙማን የተሻለ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

አሁን ላይ የሚመሩት ድርጅት ድጋፍ በዘውዲቱ፣ በምኒልክና በጳውሎስ የሕክምና ተቋማት የሚገኙ 210 ሕሙማን ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ናቸው።

ይሁን እንጂ በግል ሆስፒታሎች አገልግሎት የሚያገኙ ሕሙማን በ15 ቀናት ውስጥ እጥበት ሲያደርጉ፣ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ተጠቁሟል። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#Ethiopia

ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ከነማሻሻያ አዋጁ ትላንትና ፀድቋል።

የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ አዋጁንና ማሻሻያ ሪፖርቱን አስመልከተው የተለያዩ የድጋፍና የተቃውሞ ሐሳብና አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ 
የምክር ቤት አባልት ምን አሉ ?

- ማሻሻያው ከአሁን ቀደም ከሥራ ባህሪያቸው አንፃር ለየት ባለ የአደረጃጀትና የአሠራር መዋቅር ተደራጅተው የነበሩ የፍርድ ቤቶችን መሰል አዋጆችን መሻሩን የወቀሱ ነበሩ፡፡

- ማሻሻያ አዋጁ ልክ ለገቢዎችና ለጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች እንደሰጠው ሁሉ፣ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባ እንደነበርም ተገልጿል።

- ሥራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በየትኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚወጡ የሥራ ማስታወቂያዎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት ሊወዳደሩ የሚችሉበት አስገዳጅ ሁኔታ በግልጽ በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ አለመቅረቡ ተነስቷል።

- የውስጥ ዝውውርን በተመለከተ አንድ የተቋም ኃላፊ ለውጤታማነት በሚል ሠራተኞችን ወደ የሚፈልግበት ቦታ አዛውሮ ማሠራት፣ ይህንን የማይቀበሉ ሠራተኞች ደግሞ መልቀቅ ይችላሉ መባሉም ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ የአሠራር ክፍተቶችን የሚፈጥር እንደሆነም ተመላክቷል።

የአብን የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ፦

" እንዲህ ዓይነት አዋጆች ሲዘጋጁ ሰፊ ዝግጅትና ውይይት ይፈልጋሉ። እንዲሁም የሠራተኞችን ሥጋት ማካተት ይገባል።

የረቂቅ አዋጁ መንደርደሪያ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኢትዮጵያን የሚመስል የሠራተኞች ስብጥር እንዲኖር ነው በሚል መገለጹ ችግር አለበት።

' ሲቪል ሰርቪሱ በአንድ ብሔር የበላይነት ተይዟል ' በሚል የቀረበ ነው። ያን ለማለት ደግሞ በሚያስችል መንገድ ተዘጋጅቶ ቀርቧል።

ሲቪል ሰርቪሱ ብቃትንና አቅምን መሠረት አድርጎ ሊገነባ ይገባል። ኮታን ወደ ማከፋፈል አይወስደንም ወይ ? ሥራን በኮታ ማደላደሉ ማቆሚያው የት ነው ?

አንድ ሠራተኛ አፈጻጸሙ ምንም ይሁን ምን ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እስከፈለገ ድረስ አንስቶ ሌላ ተቋም ላይ በተመሳሳይ ደረጃና ደመወዝ መመደብ ይችላል። ያን የማይፈልግ ከሆነ ሠራተኛው መልቀቅ ይችላል መባሉ የሠራተኞችን መብት የሚጋፋና ዕጣ ፋንታቸውን በአለቆቻቸው እንዲወሰን የሚያደርግ ነው።

እንዲሁም ከሥራ እንዲለቁ የሚገፋፋ ነው።

የሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ጉዳይ ከ39 ወደ 48 ሰዓታት እንዲያድግ መደረጉም አግባብነት የሌለው ነው " ብለዋል።


የኢዜማ አባል አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) ምን አሉ ?

" በረቂቅ አዋጁ ' ዘመናዊና ኢትዮጵያን የሚመስል ' መባሉ በዘወርዋራው የኮታ ሥርዓትን የሚመለከት ነው።

' ዘመናዊ አገርና ዘመናዊ ቢሮክራሲ እንፈጥራለን ' እያልን የመንግሥት ሠራተኞችን ከችሎታና አቅም ይልቅ በብሔር ኮታ እንቅጠር ማለት እርስ በርሱ የሚቃረን ሐሳብ ነው።

ማይክሮሶፍትን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት በአሜሪካውያን ሳይሆን በህንዳውያንና በቻይናውያን የሚመሩና የሚተዳደሩ ናቸው።

የመንግሥት ተቋማት የሃይማኖት የስብከት ቦታዎች እየሆኑ ነው። ይህ በጥብቅ ሕግ ጭምር ሊከለከል ይገባል።

አንድን ሠራተኛ መሥሪያ ቤቱ ወይም የበላይ ኃላፊው በፈለገው ቦታ መድቦ ማሠራት ይችላል የሚለው ሰው በሙያ (ፕሮፌሽን) እንዳያድግና የካበተ ልምድ እንዳይኖረው እንደሚያደርግ፣ ይህ ደግሞ በተቃራኒው ቢሮክራሲውን የበለጠ የሚጎዳ ነው።

የበላይ አመራሩ የመጨረሻ ወሳኝ መሆኑ ከሕግና ከሥርዓት የሚፃረርና ሰብዓዊ መብትንም የሚጋፋ ነው።

ይህ ከሆነ ባርነትን እንደገና በሕግ እያፀደቅን ነው ማለት ነው ? ውሳኔውን ፍርድ ቤት መስጠት አለበት " ብለዋል።


የምክር ቤት አባል አቶ ለማ ተሰማ ምን አሉ ?

" ረቂቅ አዋጁ ሠራተኞች በትምህርት መስክና ደረጃቸው እንዲሁም በልምዳቸው እንጂ፣ ከዚያ ውጪ የሚመደቡበትን አሠራር አይፈጥርም።

የሚነሱ ሥጋቶች ቀጥለው ሊወጡ በሚችሉ ደንቦች ሊመለሱ ይችላሉ።

በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ አንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦች በጥርጣሬ ሊታዩ አይገባም። ሲቪል ሰርቪሱ መለወጥ አለበት። ትናንት የነበረው አግላይ ነበር። ዕድልንም አይሰጥም ነበር።

ረቂቅ አዋጁ ሁሉንም ጠርጎ የሚያስወጣ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በብቃቱ ተወዳድሮ ሠራተኛ መሆን የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው። "


ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ምን አሉ ?

🔴 ብዙዎቹ ጥያቄዎች በውይይት ወቅት ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸው ነበር።

🔴 ፍርድ ቤቶች በልዩ ሁኔታ መታየት ነበረባቸው መባሉ በረቂቅ አዋጁ በሚቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ በኩል ራሱን ችሎ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።

🔴 በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ኮታ የሚል ነገር የለም። ኮታ ተቀባይነት እንደሌለው በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተቀምጧል።

🔴 ረቂቅ አዋጁ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩትን እንደ አዲስ የብቃትና ሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት በሚል ስያሜ አቋቁሞ ሠራተኞችን በብቃታቸውን ለመመዘን ያስችላል።

🔴 ሠራተኞችን የማዘዋወሩ ኃላፊነት በማኔጅመንት እንጂ በበላይ ኃላፊዎች ብቻ አይወሰንም። የሠራተኛው ምክንያት የሚደመጥበትና መብቱ የሚጠበቅበት አሠራር በረቂቅ አዋጁ ተካቷል።

ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት ይህ ረቂቅ አዋጅ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ሆኖ በ3 ተቃውሞ በአራት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡#ሪፖርተር

@tikvahethiopia