TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
የግንቦት 2016 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ #ረቡዕ ይከፈታል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓመት ሁለት ጊዜያት ከሚካሔዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤያት አንዱ የግንቦት 2016 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ…
#Update #EOTC

" የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻ አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ ፤ የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው " - ቅዱስነታቸው

ግንቦት ወር ላይ የሚካሄደው ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተጀመረ።
 
የጉባኤውን መጀመር አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው ምን አሉ ?

ቅዱስነታቸው ፥ " ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ተለይታ አታውቅም  " ሲሉ ገልጸዋል።

ፈተናው ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ እንደሚከባትም አመልክተዋል።

" የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻ አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ " ያሉ ሲሆን " የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው " ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች ሲሉ ገልጸዋል።

የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት እንደሆኑ አሳውቀዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ ፥ " ከጥንት ጀምሮ የነበረ ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቶአል፤ በምትኩ ፦
° ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሦአል፤
° መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣
° ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጐደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን #ተሰሚነትና #ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው " ብለዋል።

" እነዚህና እነዚህ የመሳሰሉ ክሥተቶች በውስጥ ሥር በሰደዱ ቁጥር ጉዳትን እያስከተሉ ነው " ያሉት ቅዱስነታቸው " ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው፤ እሽቅድምድሙም በዚህ ዙሪያ አይሎአል " ሲሉ ገልጸዋል።

" የፈተናው መንሥኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለሱ ምቹ ሆነው መገኘታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ፈተና የማይናቅ ጉዳት እየደረሰባት ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላምዋና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቆአል " ሲሉም አሳውቀዋል።

ቅዱስነታቸው፤ " በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም " ያሉ ሲሆን " ችግር ሲኖር በመወያየት በጥበብና በሕግ ማረም እንጂ የጋራ ችግርን ለተወሰነ አካል በመለጠፍና እሱን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ንጹህ መሆን አይቻልም " ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት አስከፊ የሆነ በደል መፈጸሙን የገለጹት ቅዱስነታቸው " አሁንም አልቆመም፤ ይሁን እንጂ በደል ዛሬ ብቻ የተጀመረ አድርገን አናስብ፤ ይብዛም ይነስ በደል ፊትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም " ሲሉ ገልጸዋል።

" በደልን በካሣና በዕርቅ በይቅርታና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቅዋማዊ ሥርዓትን ማበጀት መልካም ፈሊጥ ይሆናል፤ በደልንና ጥፋትን ምክንያት አድርገን እስከ ዘለቄታው መለያየትን መምረጥ ግን ራስን በራስ መጉዳት ይሆናል " ሲሉም አስገንዝበዋል።

ጉባኤውም በዚህ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ስራ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

(የቅዱስነታቸው ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia