TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#Update

የተሻሻለው የ " ንግድ ሕግ ማስፈጸሚያ መመርያ " ሊወጣ ነው !

ከስልሣ ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ የወጣውን አዲሱን የንግድ ሕግ ማስፈጸሚያ መመርያዎች ውስጥ እና የመጀመርያው የሆነው በዚህ ዓመት ፀድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የንግድ ሕጉ ማስፈጸሚያ ይሆናል የተባለው ይህ የመጀመርያው መመርያ የ " አክሲዮን ማኅበራት " ን የሚመለከት ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ፤ " የአክሲዮን ማኅበራት ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር መመሪያ " በሚል የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቁ በዚህ በጀት ዓመት ይፀድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

መመርያው ምን ይዟል ?

- በንግድ ሕጉ ላይ " የመተዳደሪያ ደንብ ያስፈልጋል ? አያስፈልግም ? " የሚለውን ጉዳይ ለማብራራትና በቀላሉ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎችና በሁሉም ፈጻሚ ተቋማት ወጥ በሆነ መንገድ እየተተረጎመ እንዲፈጸም ለማስቻል በሚረዳ መልኩ በመመርያው እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡

- መመርያው አክሲዮን ማኅበራት ሲደራጁ ገንዘብ ከሕዝብ የሚሰበሰብበት መንገድ ላይ ምን መሆን እንዳለበት በግልፅ ያመላክታል። ኅብረተሰቡ እንዳይበዘበዝ እንዴት መተዳደር እንዳለበት በዝርዝር የተቀመጡ አንቀጾችን አካቷል፡፡

አደራጆች የምሥረታ ሒደት ለማካሄድ የሚያስከፍሉት አስተዳደራዊ ወጪ የሚዋጣው ገንዘብ ከአምስት በመቶ መብለጥ እንደሌለት በረቂቅ መመርያው ተመላክቷል፡፡

በምሥረታ ሒደት ከፈራሚዎች አስተዳደራዊ ወጪን ለመሸፈን ገንዘብ የተሰበሰበ እንደሆነ፣ ማኅበሩ ሲመሠረት የምሥረታ ወጪን ለማኅበሩ ማስተላለፍ የሚቻለው የተሰበሰበው አስተዳደራዊ ክፍያ የምሥረታ ወጪውን ለመሸፈን ያልበቃ መሆኑን የምሥረታ ኦዲተር ካረጋገጠ ብቻ ነው።

በምሥረታ ኦዲተር ሪፖርት መሠረት ለአስተዳደራዊ ወጪ ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ጥቅም ላይ ያልዋለ ቀሪ ገንዘብ ያለ እንደሆነ ማኅበሩ ሲመሠረት ፣ ለማኅበሩ ገቢ መደረግ ይኖርበታል። ይህም ቀድሞ ለአገልግሎት ተብሎ የተሰበሰበን ገንዘብ ከብክነት ያድናል።

- አደራጆች በአክሲዮን ምሥረታ ወቅት ከፈራሚዎች ሚሰበሰበውን መዋጮ በባንክ በዝግ ሒሳብ ሲያስቀምጡ በገበያው ላይ ካለው የወለድ ምጣኔ አንፃር ተመጣጣኝ የሆነ ወለድ እንዲያፈራ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

- የማኅበሩ ምሥረታ በስኬት የተጠናቀቀ እንደሆነ ዋና ገንዘቡና ያስገኘው ወለድ ለማኅበሩ ገቢ መደረግ አለበት።

- የግል አክሲዮን ማኅበር ሚመሠረተው በመሥራቾች እንደሚሆን ይደነግጋል። መሥራቾች በባለአክሲዮንነት ከሚያገኙት መብት ውጪ በመሥራችነታቸው ምክንያት የሚከፈላቸው የአገልግሎት ክፍያ አይኖርም።

- በአክሲዮኖች ላይ #ከአንድ_መቶ_ብር (100) ያነሰ ዋጋ የተጻፈባቸው አክሲዮኖች ያላቸው ማኅበራት፣ ይህ መመርያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ ቢያንስ ወደ አንድ መቶ ብር በማሳደግ መመሥረቻ ጽሑፋቸውን አሻሽለው ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።

- የአክሲዮን ኩባንያዎች የሚያደራጁ ሰዎች ያለባቸው ኃላፊነት ምንድነው የሚለውም በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በአዲሱ የንግድ ሕግ የአክሲዮን ኩባንያዎች የኤሌክትሮኒክስ ስብሰባ ማድረግ የሚችሉ በመሆኑ፣ ይህንን ለማስፈጸም ዝርዝር ጉዳዩ በዚህ መመርያ ተገልጿል።

" የቦርድ ስብሰባ " የሚደረግበት የኤሌትሮኒክ ዘዴ የተሰብሳቢዎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል ፤ የውይይቱን የድምጽ ቅጂ በትክክል መያዝ የሚችል መተግበሪያ ያለውና ፤ ሚስጢራዊነትንም መጠበቅ የሚችል መሆን አለበት።

በመመስረቻ ጽሑፍ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በስተቀር እያንዳንዱ የቦርድ አባል በዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ በአካል የመገኘት መብት ያለው ሲሆን፣ የቦርድ ስብሰባን በኤሌትሮኒክ ዘዴ ለመሳተፍ ዳይሬክተሩ ጥያቄ ካላቀረበ በቀር፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊያስገድድ ወይም በአካል የመሳተፍ መብቱን ሊገድብ እንደማይችች ተቀምጧል፡፡

- ከመመርያው መውጣት በኋላ ብዙ አክሲዮን ያላቸው ኩባንያዎች በቀላሉ ስብሰባቸውን እንዲያካሂዱ ዕድል ይሰጣቸዋል።

- የአክሲዮን ዝውውሮችን በተመለከተ በዚህ መመርያ ግልጽ ድንጋጌ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በተለይ የግለሰብ አክሲዮንን ለማስተላለፍ #የትዳር_አጋር_ስምምነት ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

"በግል የአክሲዮን ማኅበር" ውስጥ በግለሰብ የተያዘ አክሲዮንን ፦
- በሽያጭ ፣
- በስጦታ ፣
- በመያዣ
- በሌላ በማንኛውም መንግድ ለማስተላለፍ በሕግ ወይም ደግሞ በመመሥረቻ ጽሑፍ ከተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ አስተላላፊው በአስገዳጅነት ያገባ ከሆነ የትዳር አጋሩ ውል ለማዋዋል እና ሰነድን ለመመዝገብ ' ሥልጣን ባለው አካል ፊት ቀርቦ ' ስምምነቱን መግለጽ አለበት።

ያላገባ ከሆነ / ከሆነች አግባብ ካለው የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ተገቢውን ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል በሚል መመርያው ይደነግጋል፡፡

- ሁሉም የአክሲዮን ማኅበራት ይህ መመርያ ተፈጻሚ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ድረገጽ ማበልጸግና በድረገጹ ላይ በሕጉ መሠረት ተገቢነት ያላቸውን መረጃዎች ማስቀመጥ አለባቸው። ይህንን ድንጋጌ የማይፈጽም የአክሲዮን ማኅበር የንግድ ፈቃዱ ሊታገድ እንደሚችልም ተደንግጓል፡፡

- አክሲዮን ለመሸጥ ስለሚወጡ #ማስታወቂያዎች በመመርያው ላይ ተቀምጧል።

ይህም ፤ " በማንኛውም በሕዝብ ማኅበር በምሥረታ ሒደት አክሲዮን ለመሸጥ በሚተላለፍ ማስታወቂያ ስለ ታሳበው የንግድ ሥራ አዋጭነት በጠቅላላው ከመግለጽ በስተቀር ስለሚያስገኘው የትርፍ መጠን በምን ያህል ጊዜ ለኢንቨስትምንት የተከፈለው ገንዘብ እንደሚመለስ ወይም ሌሎች በተጨባጭ ሊረጋገጡ የማይችሉ መረጃዎችን መስጠት አይቻልም " በሚል ተጠቅሷል፡፡

በማንኛውም #ዋና_ገንዘብ በማሳደግ ሒደት በግል ማኅበር ወይም በሕዝብ ማኅበር፣ ለሕዝብ አክሲዮን ለመሸጥ የሚደረግ ማስታወቂያ ማኅበሩ አስቀድሞ ያገኘውን ትርፍ የሚገልጽ ከሆነ፣ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ዓመታት የትርፍ ውጤት መግለጽ ግዴታ አለበት፡፡

ነገር ግን ማኅበሩ #ለወደፊት የሚኖረውን አትራፊነት በቁጥር ወይ በመጠን መግለጽ አይቻልም።

ሚኒስቴሩ (ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር) ወይም አግባብ ያለው ሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አሳሳች ናቸው ብሎ ከወሰነ፣ አክሲዮን ለመሸጥ ለሕዝብ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች እንዲቋረጡ ለማዘዝ ይችላል።

.
.
.

መመርያው በአጠቃላይ ከአክሲዮን ምሥረታ ጀምሮ እስከሚፈርስበት ጊዜ ድረስ #ዝርዝር የአሠራር ጉዳዮችን በመተንተን የቀረበ ነው።

በአዲሱ የንግድ ሕግ መመርያ የማውጣት ሥልጣን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡

መመርያን ያዘጋጀው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሲሆን በተለይ #የሕዝብን_ገንዘብ ተቀብለው የሚያስተዳድሩ የአክሲዮን ማኅበራት ላይ መጠነኛና ቁጥጥር ለመዘርጋት የሚያስችል ነው፡፡

(ሪፖርተር ጋዜጣ የረቂቅ መመርያው ዝግጅት ተሳታፊ የሕግ ባለሙያ አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስን ዋቢ በማድረግ ያወጣው)

@tikvahethiopia