TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.8K photos
1.44K videos
207 files
3.99K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
#አማራ : ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው " ተፋላሚ ኃይሎች ሲቪል ሰዎችንና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሊቆጠቡ፣ መንግሥት የማኅበራዊ አገልግሎቶች እዲቀጥሉ አስቻይ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል። " በአማራ ክልል ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ የተላከልን መግለጫ ከላይ ተያይዟል። መግለጫው በክልሉ በተለያዩ…
#አማራ

በአማራ ክልል ለወራት ከቀጠለው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ በርካቶች በድሮን ጥቃት መገደላቸው እና በክልሉ ከፍርድ ውጭ ግድያዎች መቀጠላቸውን ዛሬ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተላከልን መግለጫ መረዳት ችለናል።

ከኢሰመኮ በደረሰን መግለጫ ፤ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል።

በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎችና ወረዳዎች በአንድ ወቅት ላይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በሌላ ወቅት ደግሞ በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር / ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው።

በግጭቱ ዐውድ ውስጥ #የአየር /#ድሮን መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት የተነሳ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን ፣ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።

ለምሳሌ ፦

- በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ፣ ' መጥተህ ብላ ' ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች #ተገድለዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

- በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት  ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

- በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል።

ኮሚሽኑ እነዚህን መረጃዎች ያገኘው የአካባቢውን ነዋሪዎች እና የዓይን ምስክሮችን በማነጋገር ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል።

በምንጃር ወረዳ ውስጥ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀያቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3ዐዐዐ የሚሆኑት አሞራ ቤቴ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሃራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል።

ለተፈናቃዮች የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡና እና በአንድ ተራድዖ ድርጅት የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደወደመ፣ ንብረታቸው እንደተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣራያ እና በር እየተነቀለ እንደተወሰደ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደተጀመረ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች አስረድተዋል።

በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጿል።

ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ ፦

- " ፋኖን ትደግፋላችሁ "

- " ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ "

- " መሣሪያ አምጡ "


- " የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ " በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎች ተገኝተዋል።

እንደማሳያ ፦

▪️በባሕር ዳር ሰባታሚት አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. #ሦስት_ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

▪️በሰሜን ጎጃም ዞን፣ አዴት ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

▪️ በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ አማኑኤል ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል።

▪️በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ ግንደወይን ከተማ ሞጣ በር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በጥይት የቆሰለን ግለሰብ እናቱና እህቱ በባጃጅ አሳፍረው ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ላይ እያሉ፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባጃጁን አስቁመው ሁሉንም ተሳፋሪዎች ካስወረዱ በኋላ " የቆሰለው እኛን ሲዋጋ ነው " በሚል ምክንያት የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራቱን ሰዎች በጥይት እንደገደሏቸው ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በባሕር ዳር፣ በፍኖተሰላም፣ በጎንደር እና በወልድያ ከተሞች በትጥቅ ግጭቱ ቆስለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ሲቪል ሰዎች እና የታጣቂ ቡድኑ አባላት በመሆን በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምናቸው እዲቋረጥ ተደርጎ #ወዳልታወቀ_ስፍራ ከተወሰዱ በኋላ ፣ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ሕክምና ተቋማቱ ሲመለሱ ቀሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጥ አልተቻለም።
 
በሌላ በኩል በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል።

ለምሳሌ ፦

መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ/ም የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከባሕር ዳር ወደ ደብረ ታቦር ሲሄዱ ' አለምበር ከተማ ' አካባቢ በታጣቂዎች ተገድለዋል።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲያመልጡ ተደርጓል። 
 
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ፤ በተለይም ከመንግሥት ተቋማት ጭምር በሚደርሱት መረጃዎች መሠረት በግጭቱ ዐውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደረጎ አርምጃ ሊወሰድበት የሚገባው ነው፡፡

የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ #2ዐዐ_የአስገድዶ_መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት ተመዝግበዋል፤ ከተጎጂዎች መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሞያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል።

ከትጥቅ ግጭቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ፦
🔹ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል የንግድ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዝርፊያ ተፈፅሟል።
🔹የማሳ ላይ ሰብል ውድመት ጨምሮ በሲቪል ሰዎች፣ በሕዝብ እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል።
🔹ሕፃናት ከትምህርት ውጪ ሆነዋል በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎት ውለዋል። ይህ ደግሞ አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ ነው።

በክልሉ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው ተቋማት በስተቀር ይህ መግለጫ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ በተለይም በግጭት ላይ ባሉ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎትም ጨምሮ ተቋርጧል።

(ዛሬ ከ #ኢሰመኮ የተላከል ሙሉ መግለጫ በዚህ ታገኛላችሁ ፦ https://t.iss.one/tikvahethiopia/82609?single)

@tikvahethiopia