TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ፦

#አማራክልል

በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ አምበላ ቀበሌ በዚገም ወረዳ ሶሪት ቀበሌ ከጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ፈጣም ሰንቶም እና በቆጣቦ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. " ኢመደበኛ " የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለጸ ቡድኖች በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል።

በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ነዋሪዎች ተፈናቅለው በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመሄድ ተገደዋል። የቀንድ ከብቶች ተዘርፈዋል።

#ቤኒሻንጉልጉሙዝ

አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ቤልሚሊ፣ አልከሻፊ እና ቤላደሩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የቤኒሻንጉል ብሔር ተወላጆች እና አብረው በሚኖሩት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ) ታጣቂ ቡድን አባላት በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በጥቃቱ 17 ሰዎች መገደላቸው ፣ አንድ ሽማግሌ ታፍነው መወሰዳቸው፣ በ7 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።

በሦስቱ ቀበሌዎች ያሉ መንደሮች በአብዛኛው የተቃጠሉና የወደሙ መሆኑን፣ የእርሻ ሰብልና የቤት እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ውድመት ደርሷል።

የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ወደ አጎራባች ቀበሌዎችና በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው መነሲቡ ወረዳ (ኦሮሚያ ክልል) ተፈናቅለዋል።

#ኦሮሚያክልል

- በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጢጆ ለቡ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በኋላ ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በፈጸሙት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃት 7 የአንድ ቤተሰብ አባላት እና 3 ጎረቤቶቻቸው ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሰዎችን ገድለዋል።

በዚያው ዕለት ታጣቂዎቹ በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ቢያንስ 12 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል።

በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ከተገደሉ 12 ሰዎች መካከል አሥራ አንዱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።

በኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው በኮኘ ቀበሌ ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የነበሩ 8 ሰዎችን ገድለዋል።

ጥቃት አድራሾች ሟቾችን ከቤት እያስወጡ #አሰልፈው_እንደገደሏቸው፣ የተወሰኑትም በቤታቸው ውስጥ እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል።

ከሟቾች መካከል #ጨቅላ_ሕፃንን ጨምሮ ነፍሰጡር ሴቶች እና ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊ ይገኙበታል፡፡

ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ተደጋጋሚ ዛቻ እየደረሳቸው መሆኑን ለኮሚሽኑ ገልጸው፤ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ተማጽነዋል፡፡

በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፣ የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን አባላት የነበሩት 9 ምዕመናን፣ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊት 8፡00 ሰዓት አካባቢ እስካሁን ማንነታቸው ባልተለዩ በታጠቁ ቡድኖች ተገድለዋል።

ግድያው የተፈፀመድ መላኮ መናሞ ቀበሌ ባለው ጫካ ውስጥ ሲሆን ገዳዮችን  አስክሬናቸውን መጣላቸው ለማረጋገጥ ተችሏል።

(የኢሰመኮ መግለጫ ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
#ቤኒሻንጉልጉሙዝ

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ወደ አዲስ አበባም ሆነ ወደ አጎራባች አካባቢዎች የሚወስደው መንገድ በፀጥታ ምክንያት ዝግ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ ሕክምና ሪፈር የሚጻፍላቸው ሕሙማን ሕክምና ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

ከአሶሳ ከተማ ተነስቶ ወደ መተከልና ኦሮሚያ ክልል የሚወስደው መንገድ በፀጥታ ችግር ምክንያት በመዘጋቱ ሕሙማን የከፋ ችግር ውስጥ ወድቀዋል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሶፊያ አወት ምን አሉ ?

- ከአጎራባች ሱዳን ፈልሰው የመጡ ስደተኞችና ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ የሠፈሩ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙት አሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል በመሆኑ፣ ሆስፒታሉ አገልግሎት ለመስጠት ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል።

- ሆስፒታሉ ከፍተኛ የሆነ የሕክምና ግብዓት እጥረት አለበት።

- ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ሕክምና እንዲያገኙ ሪፈር የሚጽፍላቸው ሕሙማን አቅም ያላቸው ብቻ የአየር ትራንስፖርት ተጠቅመው የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ነው።

- በክልሉ አብዛኛውን ነዋሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ከተማም ሆነ ወደ ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች በአየር ትራንስፖርት ሄደው ለመታከም የገንዘብ ችግር ስለሚገጥማቸው ሞታቸውን የሚጠባበቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቁጥር አንድ ከሚባሉት ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት በቀን ከ150 በላይ ለሆኑ ሕሙማን አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

- ለሆስፒታሉ የሚቀርበው መድኃኒትና ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት ጭራሽ የማይመጣጠን ነው።

- በፀጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒት እየቀረበ ያለው በአየር ትራንስፖርት ነው።

- በአየር ትራንስፖርት መድኃኒት ቢመጣም ቶሎ ቶሎ የሚያልቅ በመሆኑ መድኃኒት ለመግዛትም ሆነ ለመድኃኒት ማጓጓዣ ሆስፒታሉ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ይገኛል።

- ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና፣ የማዋለድ፣ የዓይን ሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን ይሰጣል።

- ከዚህ በፊትም የፀጥታ ችግር ባልነበረበት ወቅት ሕሙማንን በፍጥነት በአምቡላንስ በማመላለስ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፤ ይሁን እንጂ የፀጥታ ችግር በክልሉ በመባባሱ አምቡላንሶች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው አገልግሎት እንደማይሰጡ ሆኗል። ከዚህ ቀደም አንድ አምቡላንስ በታጣቂ ኃይሎች መቃጠሉንና ውስጥ የነበሩ ሕሙማንና ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለም ደበሎ ምን አሉ ?

* በክልሉ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት ሆፒታሎች አሉ፡፡ ሆስፒታሎቹ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የግብዓት ችግር ገጥሟቸዋል።

* በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረዋል።

* የመድኃኒትም ሆነ ሌሎች የሕክምና ግብዓቶችን በተመለከተ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በአየር ትራንስፖርት እያስገባን ቢሆን ችግሩ ግን ከፍተኛ ነው።

* በክልሉ የሕክምና አገልግሎቶች የሚሰጡ ሆስፒታሎች ለሕሙማን ሪፈር ሲጽፉ አብዛኞቹ ሕሙማን በአየር ትራንስፖርት ሄደው ለመታከም ይቸገራሉ፤ በዚህ ምክንያት እዚያው ሕክምናቸውን ለመከታተል ተገደዋል።

ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ

@tikvahethiopia