TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ክፍል 1-ኃላፊነት የጎደለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚያስከፍለው ዋጋ!

ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የዴሞክራሲ ማዕከላዊ መርህ ነው፡፡ ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ #መብት ደግሞ በይበልጥ እንዲተገበርና እንዲከበር ካደረጉ የታሪክ ክስተቶች፣ የቅርብ ጊዜውና ትልቁ ተጠቃሽ የማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ በባህርይው በማዕከላዊነት የሚደረግ የይዘት ቁጥጥር ባለመኖሩ፣ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ጉዳይ ያለማንም ገምጋሚነትና አርታኢነት በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ተጠቃሚ ተከታዮቻቸው በአነስተኛ ወጪ ያስተላልፋሉ፡፡ ይህም ሳንሱር እንዲጠፋ የሚደረገው ትግልና ክርክር እርባን አልባ እንዲሆን በማድረግ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እሳቤ፣ ይህን ያህል ይሄዳል ተብሎ ያልተጠበቀበት ደረጃ አድርሶታል፡፡

በዚህም ምክንያት የማኅበራዊ ሚዲያው ለዴሞክራሲ ልምምድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንደሚጫወት ዕሙን ነው፡፡ ዛሬ አንድ ግለሰብ በስልኩ የሚያደርገው ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ሮናልድ ሬገን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሳሉ ያደርጉት ከነበረው እንደሚልቅ፣ ከ20 ዓመታት በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቢል ክሊንተን ያገኙት ከነበረው መረጃ የበለጠ አንድ የ13 ዓመት ታዳጊ በስልኩ እንደሚያገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መረጃ ኃይል ነውና በዚህ ዘመን በቀላሉ የሚገኝ መረጃ ለዴሞክራሲ ልምምድ ብሎም በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ለመስጠት ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ከመሪዎቹ የሚገዳደር መረጃ እጁ ጫፍ ላይ የያዘ ዜጋ የመንግሥትት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ይችላልና፡፡ ከአንድ የዓለም ጫፍ የተከሰተን ጉዳይ  ማግኘትና መተንተን፣ ከዚያም ለውሳኔ መዘጋጀት ከኢንተርኔት ዘመን አስቀድሞ የደኅንነት ተቋማት ተግባር ነበር፡፡ አሁን ግን ከደኅንነት ተቋማት በማይተናነስ ደረጃ ማንኛውም ዜጋ መረጃ አለው፡፡ ይህም መንግሥት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች እየተከታተሉ ለምን? እንዴት? ለማን ተወሰኑ? በሚሉ ጥያቄዎች ማረምና ተጠያቂነትን ማምጣት ይቻላል፡፡

ይሁንና በ1980ዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሬገንና ከ20 ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ሥልጣን ላይ የነበሩት ክሊንተን ያገኟቸው የነበሩ መረጃዎች፣ አሁን ላይ ማንም ከሚያገኛቸው መረጃዎች የሚለዩበት አንድ ነጥብ አለ፣ ተዓማኒነት፡፡ ፕሬዚዳንቶቹ ለሚያስተላልፏዋቸው ውሳኔዎች እንዲረዷቸው መረጃዎቹን ከታማኝ ምንጮች ያገኛሉ፡፡ ለመተንተን ይረዳቸውም ዘንድ ከባለሙያዎች ጋር ይነጋገራሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ከስልኮቻችን፣ በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ የምናገኛቸው መረጃዎች ተዓማኒነታቸው አናሳ በመሆኑ የሚተላለፉ ውሳኔዎች አደገኛ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡

ለዚህ የቅርብ ጊዜ ማሳያ የሚሆነው በማይናማር (በርማ) በሮሂንጂያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመው #ግድያ ነው፡፡ በዚህች የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር የሚኖሩና እንደ አገሪቱ ዜጎች የማይቆጠሩት የሮሂንጊያ ማኅበረሰብ እ.ኤ.አ. በ2016 በአገሪቱ ወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ሲሞቱባቸው፣ ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ በቅተዋል፡፡ በዚህች አብዛኛው ማኅበረሰብ #ዜናም ሆነ ተያያዥ መረጃዎችን ከማኅበራዊ ገጾች በተለይም #ከፌስቡክ እንደሚያገኝ በሚገለጽባት አገር፣ በሮሂንጂያ ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመው በደል ‹በዓለማችን እጅግ በጣም የተጨፈጨፉ ሰዎች› በመባል እንዲታወቅ ያደረገ ጥፋት እንዲፈጸም ያደረገው #በፊስቡክ የሚለቀቅ መረጃ ነበር፡፡

በማይናማር የቡድሂስት መነኩሴ የሆኑት #አሺን_ዊራቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተከታይ ያላቸው ሲሆኑ፣ ይኼንን የተከታዮቻቸውን መብዛት ለበጎ ሳይሆን የውሸት መረጃዎችን በማሠራጨት ለበርካቶች #ሞት መንስዔ ሆነዋል፡፡ እኚህ የማይናማር ቢን ላዲን በመባል የተሰየሙት መነኩሴ ለተከታዮቻቸው ሙስሊም የሆነ አንድ ባለድርጅት አሠሪ፣ የቡድሂስት እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ደፍሯል የሚሉ የሐሰት ማስረጃ ቢያስራጩም ተጠያቂ አልሆኑም ነበር፡፡ ፌስቡክም በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢደረግለትም እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ድረስ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ከፍተኛ ጥፋት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል፡፡

በዚህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በተንሰራፉበት ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉና አብዛኛው ኅብረተሰብ ያልተማረ በሆነባቸው አገሮች፣ የማይናማር ዕጣ ፈንታ ሊደገምባቸው እንደማይችል ማረጋገጫ እንደሌለ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ይህ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፈር ካልተበጀለት #አጥፊነቱ ሊከፋ ይችላልም ይላሉ፡፡
.
.
ክፍል ሁለት 6:00 ላይ🔄

ምንጭ፦ ሪፖርተር
@tsegabwolde @tikvahethiopia