TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.8K photos
1.44K videos
207 files
3.99K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#DrAbrhamBelay

የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትግርኛ ቋንቋ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ምን አሉ ?

- ሁሉም ክልሎች እና የፌደራል መንግስት ተቋማት ለትግራይ መልሶ ማቋቋም እንዲረዱ ፣ ትምህርት ጨምሮ ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች እንዲጀምሩ ያስቻለው የፕሪቶሪያው የሰላም ውል ነው ፡፡ ስለሆንም የፕሪቶሪያው የሰላም ውል አሁንም በቦታው ነው ያለው።

- ከጦርነቱ በፊት የነበረው #ግጭት_ቆስቋሽ ሁኔታ እና አካሄድ ወደ ጦርነት እንዳይሸጋገር ለማድረግ በፌደራሉ መንግስት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ክልሉን ይመሩ የነበሩ ሰዎች ሁኔታውን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ጦርነቱ በትግራይ #አመራሮች እና #ኤሊቶች ገፋፊነት ከተጀመረ በኋላም ጦርነቱ ቆሞ ወደ ውይይት እንዲገባ ጥረት ተደርጓል። ጦርነቱ ውድመቱ እንዳይባባስ በድብቅም ይሁን በግላጭ በርካታ ውይይቶች ቢካሄዱም ሊሳካ አልቻለም።

- ጦርነቱ ተከትሎ በተለይም ከትግራይ ውጪ በመላ አገሪቱ ውስጥ የነበሩ ባለሃብቶች ፣ የመንግስት ሰራተኞችና በሌላ ስራ የተሰማሩ ከስራ ውጪ የሆኑበት ፣ የታሰሩበት ፣ ንብረታቸው በርካሽ በመሸጥ እንዲሰደዱ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ይህን እንዲቆም የፌደራል መንግስት ባደረገው ሰፊ ጥረት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ብዙ አላሳፈላጊ ነገሮች ማቆም ተችሏል።

- " በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከኔ በላይ ደስተኛ ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱ ስምምነቱ ብዙ ነገሮችን ከማባባስ ታድጓል፡፡ በፌደራል መንግሥት በኩል ስምምነቱን የፈረሙ የመንግስት ልኡካን ጀግኖች ናቸው፡፡ ምክንያቱ እንደ አገር ሊቀጥል የነበረው የስውና የንብረት ኪሳራ እንዲቆም ያደረጉ ናቸውና፡፡ "

- የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሁሉም የትግራይ ችግሮች ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ስምምነቱ እንደ አገርና ትግራይ ብዙ ጥፋቶችን አስቁሞልናል፡፡ ስምምነቱ በመፈረሙ ምክንያት ተኩሶ ቆሞ ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ሆኗል፡፡ ትልቁ የስምምነቱ ትሩፋት ይህ ነው።

- ከተወሰኑት በቀር በርካታው የትግራይ አከባቢዎች በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ነበር። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የአከካቢው አስተዳደር ተረክቧል። አሁን የተቀሩት አከራካሪ የሚባሉ ቦታዎች ናቸው። እነዚህም ተጨማሪ ግጭትና ደም መፋሰስ እንዳያስከትሉ በማሰብ በፌደራል መከላከያ ሰራዊት ስር እንዲቆዩ ተደርጓል።

- በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዚያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያው የሰላም ውል ውጤት ነው። ሁሉም ክልሎችና የፌደራል መንግስት ተቋማት ለክልሉ እንዲረዱ ፣ ትምህርት ጨምሮ ሁሉም የመንግስት አገልግሎት እንዲጀምሩ ያስቻለው የፕሪቶሪያው የሰላም ውል ነው ፣  ስለሆንም የፕሪቶሪያው የሰላም ውል አሁንም በቦታው አለ።

- ስምምነቱ ከውል በላይ በሁለቱ ተወያዮች በኩል መተማመን እንዲፈጠረ ያበረከተው አስተዋፅኦ ስምምነቱ ከስምምነት በላይ መሆኑ አንድ አመላካች ተደርጎ ይወሰዳል።

- የእርሻ እና የኢንዳስትሪ ስራ እንዲነቃቃ የሚያግዝ የማሽነሪና የውጭ ምንዛሪ መሰጠቱ፣ የክልሉ የትምህርትና የጤና ተቋማት መልሶ የመገንባት ሂደት እንዲፋጠን ያስቻለው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ውጤት ነው።

- የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የፌደራል መንግስት የሚመራውን የብልፅግና ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የፓለቲካ ፓርቲዎች የተካተቱበት አሳታፊ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ቢደነግግም ፣ የፌደራል መንግስትና የብልፅግና ፓርቲ በሆደ ሰፊነትና ለሰላም ካለቸው ፍላጎት በሚመነጭ ክልሉ ሃላፊነት ወስዶ በፍጥነት ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት እድል መሰጠቱ ሊመሰገንና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

- ከትግራይ ምዕራባዊና ደቡባዊ ዞኖች የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቄያቸው የመመለስ ጉዳይ መዘግየቱ አለ የሚባል ቢሆንም የተዘነጋ እንዳልሆነ ግን ሊሰመርበት ይገባል። የፌደራል መንግስት ፍላጎት ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ይህ አቋሙም ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ውል ማግስት ጥረት ከማድረግ ባሻገር 2015 ዓ.ም ክረምት እንዲመለስ ፍላጎት ነበር። ይሁን እንጂ በአፈፃፀም መዘግየት ምክንያት እስከ አሁን አልተሳካም።

- ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው የመመለስ ጉዳይ ዳግም ወደ ጦርነት በማይመልሰን መልኩ መፈፀም አለበት የሚለው አቅጣጫ ተቀምጦ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ጥያቄዎች በሚነሳባቸው አከባቢዎች ያሉ ታጣቂዎች ትጥቃቸው እንዲፈቱ የማድረግ ስራ እየሰራ ነው። ቢሆንም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ወደ አከባቢው አልተመለሰም የፌደራል መንግስት አቋም ህዝቡ ወደ ቄየው ተመልሶ የራሱ አመራሮች መርጦ በአመቺ ጊዜ በአከባቢው ህዝብ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረግ ነው።

- የፌደራል መንግስት አቋም ግልፅ ነው ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ይመለሱ ፣ ራሳቸው በመረጡዋቸው መሪዎች ይተዳደሩ ፣ የህዝበ ውሳኔው ጉዳይ ጊዜ ሲደርስ የሚከናወን ይሆናል። አሁንም አቅጣጫው እንዲፈፀም በመጠባበቅ ላይ ነን ፣ ዳግም ግጭት ሳይፈጠር ከዚህ በላይ የተሻለ አማራጭ አለኝ የሚል ካለ ደግሞ የፌደራል መንግስት ለማዳመጥ ዝግጁ ነው። 

- የሻብዕያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ መሬት ስለመውጣት ጉዳይ ምን አሉ ? 👉 "  ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በፊት በበርካታ የትግራይ አከባቢዎች የሻዕብያ ሃይል ገብቶ ነበር ፣ ከስምምነቱ በኋላ እንዲወጣ ተደርጓል ፣ አሁንም የተቀሩ ቦታዎች ካሉ ቦታዎቹ እና ቀበሌዎች ከፌደራልና ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ቡድን በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብና መፍትሄ እንዲሰጠው እየሰራን ነው ሁሉም ልክና መስመር ይይዛል። "

- በትግራይ የተከሰተው ድርቅ እና ረሃብ በተለመደው አካሄድ ይፈታል የሚል እምነት የለንም ፣  እርግጥ ነው ወደ አከባቢው መድረስ ያለበት የሰብአዊ ድጋፍ እየደረሰ ነው ፣ እየተላከ ያለው ድጋፍ ወደ ተጠቃሚው መድረሱ ማረጋገጥ እንዳለ ሆኖ ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና የፈደራል የመንግስት ተቋማት እገዛ በማድረግ ችግሩ በመፍታት እንዲረባረቡ አቅጣጫ ተቀምጧል።

- በትግራይ የተከሰተው ድርቅ እና ረሃብ በዘላቂነት የሚፈታ ከፌደራልና ከክልሉ የተውጣጣ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል። ይህንን ግብረ ሃይል የሚያቀርበው ጥያቄ ለመመለስ ሁሉም የትግራይ ተወላጆችና መላ ኢትዮጵያውያን ዝግጁ እንዲሆኑ ከወዲሁ ጥሪ እናቀርባለን።

ቃለ ምልልሱን ተከታትሎና ወደ አማርኛ ትርጉም መልሶ ያቀረበው የመቐለ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው፡፡

#TikvahMekelleFamily

@tikvahethiopia